ኮሮናቫይረስ፡ በቫይረሱ ምክንያት 2.5 ሚሊዮን ታዳጊዎች የመዳር አደጋ ተጋርጦባቸዋል

ሴት ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ያለ እድሜያቸው የሚዳሩ ሴት ልጆች ቁጥርን ከፍ ያደርጋል ተባለ።

ባለፉት 25 ዓመታት ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የተደረገውን ጥረት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወደኋላ እንደመለሰው የህጻናት አድን ድርጅቱ ሴቭ ዘ ችልድረስን አስታውቋል።

ድርጅቱ እስከ ጎሮጎሳውያኑ 2025 ድረስ ኮሮናቫይረስ 2.5 ሚሊዮን ህጻናት ገና በለጋ እድሜያቸው እንዲዳሩ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብሏል።

ወረርሽኙ ድህነት እየጨመረ፤ ህጻናትን ከትምህርት ውጪ እያደረገ ለጉልበት ብዝበዛ እና ለትዳር እያጋለጣቸው ነው ብሏል ሴቭ ዘ ችልድረን።

በደቡብ እስያ፣ አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ የሚገኙ ሴት ህጻናት ደግሞ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው ተብሏል።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው ድርጅት መንግሥታት ሴት ህጻናት ያለ እድሜያቸው እንዳይዳሩ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።

"መሰል ጋብቻዎችን የሴቶችን መብት የሚጥሱ፣ ለድብርት እና ጥቃት የሚያጋልጡ ከፍ ሲልም ለሞት የሚዳርጉ ናቸው" ሲሉ የድርጅቱ የህጻናት ጥበቃ አማካሪ ካረን ፍላንጋን ተናግረዋል።

በመላው ዓለም በየዓመቱ 12 ሚሊዮን ህጻናት ያለ እድሜያቸው እንደሚዳሩ የሴቭ ዘ ችልድረን አሃዝ ያመላክታል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስን ተከትሎ ያለ እድሜያቸው የሚዳሩ ልጆች ቁጥር እንደሚጨምር ተገምቷል።

በጎሮጎሳውያኑ 2020 ላይ ብቻ 500ሺህ ሴት ልጆች ተገደው የተዳሩ ሲሆን ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴት ልጆች ደግሞ ያረግዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

መንግሥታት እና ድርጅቶች አስፈላጊውን እርምጃ ካልወሰዱ በ2025 ላይ ያለ እድሜያቸው የሚዳሩ ልጆች ቁጥር ከ61 ሚሊዮን በላይ ይሆናል ሲል ድርጅቱ አስጠንቅቋል።

ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግሥታት የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ በቀጣዩ 10 ዓመታት ያለ እድሜ የሚዳሩ ልጆች ቁጥር ከ13 ሚሊዮን ይሻገራል ብሎ ነበር።