ኮሮናቫይረስ፡ የኮቪድ-19 ውጤትን በ30 ደቂቃ ውስጥ ማወቅ ሊቻል ነው

ቅስቀሳ ሲደረግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ኮቪድ-19ን በደቂቃዎች ውስጥ የሚለይ ምርመራ በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመለየት ስራን በእጅጉ ያሳድጋል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ተናገረ።

አምስት ዶላር ብቻ የሚያስወጣው ይህ ምርመራ ሃብታም ባልሆኑ እና የጤና ባለሙያዎችና የላብራቶሪ እጥረት ባለባቸው አገራት የኮቪድ-19 ሕሙማንን ለመለየት በእጅጉ ይረዳል ተብሏል።

መመርመሪያውን ከሚያመርቱ ድርጅቶች ጋር የተደረገ ስምምነት በስድስት ወር ውስጥ 120 ሚሊዮን መመርመሪያዎችን ለማምረት ያስችላል።

ይህንን እርምጃ የጤና ድርጅቱ የበላይ ኃላፊዎች "ጉልህ ሚና የሚጫወት" ብለውታል።

በበርካታ አገራት ምርመራ ከተደረገ በኋላ ውጤት ለማወቅ የሚፈጀው ጊዜ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያርጉትን ትግል ጎድቶት ቆይቷል።

እንደ ሕንድና ሜክሲኮ ባሉ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ በተሰራጨባቸው አገራት በፍጥነት መርምሮ ውጤቱን ማወቅ አለመቻል የወረርሽኙን የመስፋፋት ፍጥነት ትክክለኛ ምስል ማሳየት አልቻለም ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ይህ አዲሱ "ተንቀሳቃሽ እና ለአጠቃቀም ምቹ የሆነ" መመርመሪያ ውጤትን ከ15 እስከ 30 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጥ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሰኞ እለት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን የኮሮናቫይረስን ውጤት ለማወቅ ሰዓታት ካልሆነም ቀናት እንደሚፈጅ ይታወቃል።

አቦት እና ኤስዲ ባዮሴንሰር የተባሉ መድሃኒት አምራቾች ከቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመሆን 120 ሚሊዮን መመርመሪያዎችን ለማምረት ስምምነት መድረሳቸውን ዶ/ር ቴድሮስ ጨምረው ገልፀዋል።

በዚህ ስምምነት መሰረት የሚመረቱ መመርመሪያዎች በቫይረሱ በጣም የተጎዱ የላቲን አሜሪካ አገራትን ጨምሮ ለ133 አገራት ይሰጣል ተብሏል።

"ይህ በተለይ ከፍተኛ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች የመመርመር አቅም ላይ ትልቅ እመርታ የሚፈጥር ነው" ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ።

አክለውም "ላቦራቶሪ በሌላቸውና ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ወይንም ምርመራውን ለማካሄድ በቂ የሰለጠነ ባለሙያ በሌለበት አካባቢ የመመርመር አቅምን ያሰፋል።''

ኮሮና
Banner