ከኤችአይ ቪ የተፈወሰው የመጀመሪያ ግለሰብ ህይወቱ አለፈ

ቲሞቲ ሬይ ብራውን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከኤች አይ ቪ ለመፈወስ የመጀመሪያ የሆነው ግለሰብ በካንሰር ህይወቱ አለፈ።

በቅፅል ስሙ "የበርሊኑ ህመምተኛ" ተብሎ የሚታወቀው ቲሞቲ ሬይ ብራውን መቅኒ (ቦን ማሮው) የለገሰው ግለሰብ ኤችአይቪ በተፈጥሮ ከማይዛቸው ጥቂት ሰዎች ውስጥ አንዱ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ ነበር ያልተጠበቀ ፈውስ የመጣለት።

ንቅለ ተከላውም የተካደበት ወቅትም በጎሮጎሳውያኑ 2007 ነበር።

ቲሞቲ የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት መውሰድ ያቆመ ሲሆን ከቫይረሱ ነፃ መሆኑንም የህክምና ባለሙያዎች አረጋግጠዋል።

የቲሞቲ ከቫይረሱ በዚህ መልኩ መፈወስም በሽታው ለወደፊቱ እንደሚድን ተስፋን የፈነጠቀ ነው በማለትም አለም አቀፉ የኤድስ ማህበረሰብ አስታውቆ ነበር።

የአምሳ አራት አመቱ ቲሞቲ ትውልዱ አሜሪካዊ ሲሆን በኤች አይ ቪ መያዙንም ያወቀው በበርሊን ይኖር በነበረበት በጎሮጎሳውያኑ 1995 ነው።

በ2007ም አኪዪት ማይሎይድ ሉኬሚያ በተባለ የደም ካንሰር አይነት መታመሙም ታወቀ።

እናም የደም ካንሰሩንም ለመፈወስ በካንሰር የተበከለውን መቅኒ (ቦን ማሮው) ማጥፋትና በሌላ መቅኒም (ቦን ማሮው) መተካት (ንቅለ ተከላ) ማድረግ ነበር።

የለጋሹ ግለሰብ ዘረመል ባልተለመደ መልኩ ኤች አይ ቪ በተፈጥሮ የማይዛቸውና የመከላከል አቅም ያለው ሲሲአር5 ተብሎ የሚጠራው መኖሩ ለቲሞቱም መፈወስ ምክንያት ሆኗል።

ይሄም ዘረ መል ቲሞቲ ቫይረሱ ከደሙ ውስጥ እንዳይኖር ረድቶታል።

ነገር ግን ለመፈወስ ምክንያት የሆነው የሉኬሚያ ካንሰር ከአመታት በኋላ በዘንድሮው አመት አገርሽቶ ጭንቅላቱን እንዲሁም አከርካሪ አጥንቱን ክፉኛ ጎድቶትም ለሞት አድርሶታል።

"በከፍተኛ ኃዘንና ድንጋጤም ሆኜ ነው ቲሞቲ ህይወቱ እንዳለፈ የምናገረው። ከአምስት ወራት ካንሰር ትግል በኋላ እኔም፣ጓደኞቹና የቅርብ ሰዎቹ አጠገቡ ባለንበት ይህቺን አለም ጥሏት ሄዷል" በማለትም የህይወት አጋሩ ቲም ሆፍጀን በፌስቡክ ገፁ አጋርቷል።

አክሎም "ቲም ከኤች አይቪ እንዴት እንደተፈወሰ በተደጋጋሚም ያወራ ነበር። ለብዙዎችም የተስፋ አምባሳደር ሆኗል" ብሏል።