ኮሮናቫይረስ፡ በሲንጋፖር ያለውን ኢፍትሀዊነት ያጋለጠው ወረርሽኝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዛኪር ሆሴይን ኮካን ነገሮች በእጅጉ እያስመረሩት መጥተዋል። ከ11 ሰዎች ጋር በጋራ ከሚኖርበት ክፍል ውስጥ እንዲወጣ ከተፈቀደለት በርካታ ሳምንታት አልፈዋል።
የሚኖርበት ክፍል በውስጡ ካሉት ስድስት የብረት አልጋዎች በስተቀር ባዶ ነው። ግላዊ ሚስጥራቸውን ለመጠበቅ ደግሞ የሚጠቀሙት ልብሶቻቸውን በአልጋዎቻቸው ዙሪያ በማሰር ነው።
'' ቀንና ሌሊት በዚሁ አንድ ክፍል ውስጥ ነው የምናሳልፈው'' ይላል ዛኪር።
'' እውነቱን ለመናገር ከፍተኛ የስነ ልቦና እንግልት እየደረሰብን ነው። በቃ እስር ቤት ውስጥ እንደመታሰር ነው የምቆጠረው'' በማለት ሁኔታውን ያስረዳል።
''አካላዊ ርቀትን ቢሆን መጠበቅ የሚታሰብ አይደለም፤ በዚህ ጠባብ ክፍል ውስጥ እንዴት ነው ይህንን ልናደርግ የምንችለው? ምንም ቦታ የለም'' በማለትም የሚኖሩበት ቦታ ጥበት አካላዊ ርቀትን የቅንጦት ያህል እንዲታሰብ እንዳደረገው ይገልፃል።
ዛኪር በኮሮረናቫይረስ መያዙ ከተረጋጋጠ በኋላ ወደለይቶ ማቆያ እንዲገባ ተደርጎ ነበር። ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ከቫይረሱ ማገገሙን ተከትሎ ደግሞ ከማዕከሉ እንዲወጣ ተፈቅዶለታል።
እነዛ በማዕከሉ ያሳለፋቸው አስቸጋሪ ቀናትም ደግመው እንደማይመጡ ነበር እሳቤው።
ነገር ግን ባለፈው ወር አንድ ስደተኞች የሚኖሩበት ማዕከል ውስጥ ኮሮናቫይረስ መገኘቱን ተከትሎ ልክ እንደማንኛውም በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞቹ በሙሉ ዛኪርም ተመልሶ ወደ ለይቶ ማቆያው እንዲገባ ግድ ሆኗል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን በሚያስጨንቅበት ወቅት ሲንጋፖር በወሰደቻቸው እርምጃዎች ስርጭቱን በመቆጣጠሯ ከፍተኛ ሙገሳ ሲቀርብላት የነበረ ቢሆንም የውጭ አገራት ሰራተኞች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሲገባ ግን ሁኔታዎች የተበላሹ ናቸው።
ምንም እንኳን በአሁኑ ሰአት አብዛኛው የሲንጋፖር ዜጋ ወደ ስራው እየተመለሰ ቢሆንም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የሌላ አገር ዜጎች ጉዳይ ግን አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።
ሲንጋፖር ውስጥ 300 ሺ የሚደርሱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የሌላ አገራት ዜጎች የሚገኙ ሲሆን አብዛኛዎቹ ከሕንድና ባንግላዴሽ የመጡ መሆናቸው ይነገራል። በብዛት ደግሞ የሚሰሩት በግንባታ እና በፋብሪካዎች ላይ ነው።
አንድ የውጭ አገር ዜጋ ሲንጋፖር ውስጥ መኖር የሚችለው ቀጣሪው ድርጅት መኖሪያ ቤት ማቅረብ የሚችል ከሆነ ነው። ስለዚህ አብዛኛዎቹ የውጭ አገር ሰራተኞች በብዛት ከሚኖሩባቸው ቤቶች በመኪና ታጭቀው ነው ወደ ስራ ቦታ የሚሄዱት። ይህ ደግሞ ለኮሮረናቫይረስ ስርጭት በር ይከፍታል።
ምንም እንኳን ደንበኛ የሆነ ሕግ ባይኖርም በአንድ ቤት ውስጥ እስከ 20 የሚደርሱ ሰዎች የሚኖሩ ሲሆን ይህም ከኮሮረናቫይረስ ወረርረሽኝ በፊት ነው።
መጋቢት ወር ላይ የስደተኞች መብት ተቆርቋሪው ድርጅት 'ትራንስየንት ዎርከርስ ካውንት' በበኩሉ ስደተኞቹ በዚህ መልክ መኖራቸው ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቅ ነበር።
ድርጅቱ ይህንን ካለ ሳምንታት በኋላ ሲንጋፖራውያን የቫይረሱን ስርጭት እየተቆጣጠርነው ማለት በሚጀምሩበት ሰአት ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ መያዝ ጀመሩ።
ይህን ተከትሎም የሲንጋፖር ባለስልጣናት ስደተኞቹ የሚኖሩባቸው ህንጻዎች እንዲታሸጉ ወሰኑ። በዚህም ምክንያት 10 ሺህ የሚደርሱ በቫይረሱ ያልተያዙ ስደተኛ ሰራተኞችን በማስቀረት በርካታ ፋብሪካዎች እንዲዘገጉና ግንባታዎች እንዲቆሙም ተደረገ።
ነገር ግን ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ስደተኞች ከመኖሪያ ማዕከላቱ እንዳይወጡ ተደረጉ።
በመቀጠልም መንግሥት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን በቀን ውስጥ መመርመሩን ተያያዘው። በቫይረሱ የተያዙትም እየተለዩ ህክምና መደረግ ተጀመረ።
በሲንጋፖር የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ አነዚህ ስደተኞች ከሚያውቁ በእጅጉ የተለየ ነው። አብዛኛው ዜጋ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እየተንቀሳቀሰ ወደ ገበያ ማዕከላት ሲሄድ ስደተኛ ሰራተኞቹ ግን ለሳምንታት ከማዕከላቱ እንዳይወጡ ተደርገው ምግብ እንኳን የሚቀርብላቸው በተመጠነ መልኩ ነበር።
ከባንግላዴሽ የመጣው ዛኪርም የዚህ ሰለባ ነው። ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በፊትም በአንድ ግንባታ ድርጅት ውስጥ በግንባታ አስተባባሪነት ይሰራ ነበር። በኮቪድ ተይዞ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ግን እንደ ሕገወጥ ስደተኛ ይስተናገድ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጿል።
'' 6 ሜትር በ7 ሜትር በሆነ ክፍል ውስጥ የምንኖረው 12 ወንዶች ነበርን። አካላዊ ርቀት ደግሞ የማይታሰብ ነው። እንዳውም እንደ ፌዝ ነው የሚቆጠረው'' ይላል
በአንድ ህንጻ ላይ ከሚገኘው ወለል ላይ ተመሳሳይ 15 ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን ቁጥሩ ሲሰላ በአንድ ወለል ላይ እስከ 180 ሰዎች ይኖራሉ ማለት ነው። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ታዲያ በጋራ የሚጠቀሙት አንድ መጸዳጃ ቤትና የገላ መታጠቢያ ብቻ ነው ያለው።
በሲንጋፖር መንግስት ሕግ መሰረት ግን አንድ መጸዳጃ ቤት ለ15 አልጋዎች ብቻ ነው የሚፈቅደው። በዚህ ጉዳይ ላይ የህንጻውን አስተባባሪዎች ቢቢሲ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ምላሽ ባለማግኘቱ አልተሳካም።
ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በርካቶች እራሳቸውን ለማጥፋት እንደሞከሩና በሰውነታቸው ላይ ጉዳት ማድረሳቸውም ተገልጿል። ሕይወታቸው ያለፈ ስደተኞችም መኖራቸውንም ሰራተኞቹ ይገልጻሉ።
በቅርቡ ደግሞ አንድ ተንቀሳቃሽ ምሰል በማህበራዊ ሚዲያ በብዛት ሲሽከረከር ነበር። አንድ ስደተኛ ሰራተኛ በመስኮት በኩል እራሱን ወደ ምድር ሊወረውር ሲሞክር ሌሎች ሰዎች ተባብረው ሲያድኑት ያሳያል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ስደተኛ ሰራተኞቹ ቤተሰባቸውን መርዳት ካለመቻላቸው ጋር በተያያዘ በርካታ ቅሬታዎችን ያነሳሉ።
''ወደውጪ መውጣት ስለማይፈቀድልን ለቤተሰቦቻችን ገንዘብ መላክ አልቻልንም። አንዳንዶች ደግሞ ከነጭራሹ ደሞዛቸው ያልተከፈላቸውም አሉ'' ይላል ዛኪር።
የሲንጋፖር የሰው ሀብት ሚኒስቴር በበኩሉ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ሁሉም የሙሉ ጊዜ ሰራተኞች ደሞዛቸው ሊከፈላቸው እንደሚገባ ያስታወቀ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ስራ ላይ ላልሆኑት ግን ወጥ የሆነ አሰራር መከተል ከባድ እንደሆነ ገልጿል።
ባሳለፍነው ወር የሲንጋፖር መንግሥት እንዳስታወቀው ሁሉም ስደተኞች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ ምርመራ መደረጉንና አካባቢዎቹ ከኮሮረናቫይረስ ነጻ መሆናቸውን ገልጿል።
ነገር ግን መንግሥት ይህን ካለ ከሳምንታት በኋላ ሰራተኛ ስደተኞቹ በሚኖሩበት አካባቢ ቫይረሱ እንደ አዲስ ማገርሸቱ ተሰምቷል።
ዛኪርም ቢሆን መቼ ከመኖሪያ ቤቱ እንደሚወጣ አያውቅም። ትልቁ ምኞቱም ነገሮች ወደቀደመ ቦታቸው ተመልሰው ወደሚወደው ስራው መመለስ ብቻ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጿል።
''እኔ እስካሁን 17 ዓመታትን በሲንጋፖር አሳልፌያለው። የሲንጋፖር አንድ አካል እንደሆንኩኝ ነው የሚሰማኝ። እንደ ዜጋ እንድንታይ አይደለም ጥያቄያችን፤ የምንፈልገው እንደ ሰው እንድንቆጠር ብቻ ነው። እንደ ማህበረሰቡ አካል እንድንታይ ነው ምኞታችን" በማለትም አስረድቷል።












