የ53 ዓመቱ ፕሮፌሽናል እግር ኳሰኛው ካዙ

የ53 ዓመቱ ፕሮፌሽናል እግር ኳሰኛው ካዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty

የምስሉ መግለጫ, የ53 ዓመቱ ፕሮፌሽናል እግር ኳሰኛው ካዙ

እርግጥነውየጃፓንሊግካፕጨዋታዎችይህንያህልየዓለምአቀፍዘገባዎችርዕስአይሆኑም።በሃገሪቱዋናውሊግየሚጫወተውዮካሃማየስፖርትክለብባለፈውወርያሰለፈውተጫዋችግንየብዙዎችንዓይንስቧል።

የዮካሃማ አምበል ካዙዮሺ ሚውራ 53 ዓመቱ ነው።

ካዙዮሺ ከክለቡ ጋር የነበረውን ውል ሲያራዝም ቢቢሲና ሴኤንኤንን ጨምሮ በርካቶች አስደናቂ ዜና ሲሉት አውርተዋል።

ሰውዬው በዕድሜ ትልቁ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የጊነስ አስደናቂ ድርጊቶች መዝገብ ላይ መሥፈር ችሏል።

ወዳጆቹ ‘ንጉስ ካዙ’ እያሉ የሚጠሩት ካዙዮሺ ማነው? እንዴትስ ይህን ሁሉ ዓመት እግር ኳስ ሊጫወት ቻለ?

ካዙ ታሪኩ የሚጀምረው 1970 [በአውሮፓውያኑ] ነው ይላል። ምክንያቱ ደግሞ ፔሌ እና የአባቱ 8 ሚሊሜትር ካሜራ።

የካዙ ቤተሰቦች እግር ኳሰኞች ናቸው። ታላቅ ወንድሙ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ነበር። አባቱ ደግሞ በእግር ኳስ ፍቅር የወደቁ ሰው ነበሩ።

“አባቴ 1970 ሜክሲኮ የተካሄደውን የዓለም ዋንጫ ለማየት ሄዶ ነበር። ጨዋታዎቹን በ8 ሚሊሜትር ካሜራው ይቀርፃቸው ነበር።”

ወቅቱ ብራዚላዊ ፔሌ የገነነበት ነበር። የካዙ አባት ፔሌ ኳሷን ሲያንቀረቅብ የቀረፁትን ይዘው መጥተው ለካዙ ያሳዩታል። ካዙም በእግር ኳስ ፍቀር ተነደፈ።

ካዙ በወቅቱ ገና የ3 ዓመቱ ልጅ ነበር። ነገር ግን አባቱ የቀዱትን የፔሌ ቪድዮ አይቶ አይጠግብም ነበር። እያደገ ሲመጣ ከብራዚል እግር ኳስ በቀር ሌላ ነገር አታሳዩኝ ይል ጀመር።

ገና ከልጅነቴ ጀምሮ እግር ኳስ በጣም እወድ ነበር። ወደፊት ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች እሆናለሁ እያልኩ እመኝ ነበር።“

የካዙ አባት ብራዚል ውስጥ ሥራ አገኙ። ቤተሰቡም ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ሳዎ ፓውሎ አመራ።

ካዙ በልጅነቱ ሳዎ ፓውሎ ውስጥ ለሚገኝ አንድ ጁቬንቱስ ለተሰኘ ክለብ መጫወት ጀመረ። ነገር ግን ሕይወት ቀላል አልነበረችም። አብረውት የሚኖሩት ዕድሜያቸው ከ15-20 የሚሆኑ ብራዚላዊያን ናቸው።

ካዙ ደግሞ ፖርቼጊዝ [የብራዚል መግባቢያ ቋንቋ] ገና አልለመደም።

“ቋንቋው ሊገባኝ አልቻለም። ባሕሉም ለኔ እንግዳ ነበር። በጣም ብቸኝነት ይሰማኝ ነበር። በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት እጅግ ከባድ ነበሩ።”

ቢሆንም ካዙ ተስፋ አልቆረጠም። በየቀኑ ልምምድ ያደርግ ጀመረ። ቋንቋ ማጥናቱንም ተያያዘው።

እንደው በእግር ኳስ ባይሳካልህ ኖሮ በምን ሙያ ትሰማራ ነበር? ከቢቢሲ ለካዙ የቀረበ ጥያቄ። ካዙ ትንሽ ከቆዘመ በኋላ “እውነት ለመናገር ምንም አላውቅም። ሁሌም ምኞቴ እግር ኳሰኛ መሆን ነበር። ይህ በጣም ከባድ ጥያቁ ነው።”

ከሶስት ዓመታት በኋላ ለሳንቶስ ፈረመ። በአባቱ ካሜራ ያየው የነበረው ፔሌ ልጅነቱን ያሳለፈበት ሳንቶስ። ካዙ ብራዚል ውስጥ ለተለያዩ ክለቦች ተጫውቷል።

ወደ ጃፓን የተመለሰው 1990 [በአውሮፓውያኑ] ነበር። 1993 ላይ ጄ-ሊግ [የጃፓን ፕሪሚዬር ሊግ] ተመሠረተ። በወቅቱ ካዙ እጅግ ውድ ተጫዋች ነበር።

በሚቀጥለው ዓመት ወደ ጣልያን አምርቶ ለጄኔዋ በመጫወት ታሪክ ሠራ - በሴሪአው የተጫወተ የመጀመሪያው ጃፓናዊ በመሆን።

በመጀመሪያ ጨዋታው ከወቅቱ የጣልያን ኮከብ ፍራንኮ ባሬሲ ጋር ተጋጭቶ ተጎዳ። ከጄኖዋ ጋር የነበረው ጊዜም ይህን ያህል ውጤታማ አልነበረም።

ወደ ሃገር ቤት ሲመለስ ግን ብዙዎች በአድናቆት ተቀበሉት።

የጃፓን የስፖርት ጋዜጠኞች ካዙ ማለት ለጃፓን እግር ኳስ መዘመን ትልቅ ሚና የተጫወተ ሰው ነው ይላሉ። አርጀንቲና ማራዶና እንዳላት ሁሉ ጃፓንም ካዙ አላት ይላል የስፖርት ጋዜጠኛው ሾን ካሮል።

ካዙ አሁን ለሚጫወትለት ዮካሃማ ክለብ የፈረመው 2005 ላይ ነው። በ38 ዓመቱ። ክለቡ በሱ መሪነት ከታችኛው ሊግ ወደ ዋናው ጄ-ሊግ በአንድ ዓመት አደገ።

ነገር ግን ክለቡ ተመልሶ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ታችኛው ሊግ ወረደ። ካዙ ግን ከክለቡ ጋር መቆራረጥ አልመረጠም።

ካዙዮሺ በሚሠራቸው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እጅጉን ይታወቃል። “እርግጥ ነው እንደ ወጣት ተጫዋቾች ለኔ ሁሉም ነገር ቀላል አይደለም። ነገር ግን እግር ኳስን በጣም ስለምወድ አደርገዋለሁ።“

ካዙ ይህን ሁሉ ዓመት በእግር ኳስ መቆየት የቻለው የሰውነት ብቃቱን በመጠበቁ ብቻ አይደለም። ባሕሪውም አስተዋፅዖ አድርጎለታል።

ብዙዎች ከሱ ጋር የተጫወቱም ሆኑ እሱ ሲጫወት የተመለከቱ ፀባዩ እጅግ መልካም እንደሆነ ተናግረው አይጠግቡም። ለዚህም ነው ጃፓናውያን እጅግ የሚወዱት ይላሉ።

በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ለሌለው ዮካሃማ የእግር ኳስ ቡድን እየተጫወተ እንኳ እሱ ይሰለፋል ሲባል ተጨማሪ 3 ሺህ 4 ሺህ ሰዎች ወደ ስታድየም ይመጣሉ።

ካዙ አሁን ለሚጫወትበት ክለብ ብዙ ጊዜ ሲሰለፍ ባይስተዋልም ክለቡ ግን ልምዱን በጣም ይፈልገዋል። ለዚህም ነው ውሉን ያራዘሙለት ይላሉ የጃፓን ስፖርት ጋዜጦች።

“መልበሻ ክፍል ውስጥ የሱ መኖር ትልቅ ለውጥ ይፈጥራል። ጃፓን ደግሞ በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች የሚከበሩባት ሃገር ናት” ይላል ጋዜጠኛው ሾን።

በዚህ ዕድሜህ እግር ኳስ ለመጫወትህ ሚስጥሩ ምንድነው የሚለው ጥያቄ ለካዙ ብርቅ አይደለም። እሱ ግን እንዲህ ይላል፤ “ምንም ሚስጢር የለውም - ጠንክሮ መሥራትና መሰጠት እንጂ።”