ላይቤሪያ፡ በጦር ወንጀል የሚፈለገው ተጠርጣሪ ለንደን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, KIRSTY O'CONNOR
በላይቤሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ተፈፅሟል በተባለ የጦር ወንጀል የተጠረጠረው ግለሰብ በለንደን በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለፀ።
የ45 ዓመቱ ግለሰብ የተጠረጠረው በአገሪቷ በጎርጎሮሳዊያኑ 1989 እና 2003 መካከል ባሉት ጊዜያት በተካሄዱት የእርስ በርስ ጦርነቶች ወቅት ፈፅሞታል በተባለ ወንጀል መሆኑን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል።
በከተማዋ የጦር ወንጀሎች ቡድን መኮንኖች ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ያዋሉት ሐሙስ ዕለት ምሽት 9 ሰዓት ገደማ መሆኑም ተገልጿል።
ቡድኑ በደቡባዊ ምስራቅ ለንደን የግለሰቡን አድራሻ ሲፈልጉ እንደነበር ጠቅሶ፤ በመጨረሻም በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተናግሯል።
እንደ ከተማዋ ፖሊስ ከሆነ ግለሰቡ የተያዘው በዓለም አቀፉ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት በ2001 ከወጣው ሕግ ጋር በሚፃረር የጦር ወንጀል ተጠርጥሮ ነው።
በላይቤሪያ በተደረጉ ሁለት የእርስ በርስ ጦርነቶች [ ከ1989-1996 እና ከ1999- 2003] 250 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን በበሺዎች የሚቆጠሩም ተፈናቅለዋል።
የአገሪቷ የቀድሞ ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለር በጎረቤት አገር ሴራሊዮን ውስጥ የጦር ወንጀል በመፈፀም በኋላ ላይ በዩናይትድ ኪንግደም ለእስር ተዳርገዋል።
የቀድሞ ፕሬዚደንቱ ቻርለስ ቴለር የላይቤሪያ 22ኛ ፕሬዚደንት የነበሩ ሲሆን ከጎርጎሮሳዊያኑ 1997 እስከ 2003 ድረስ ማለትም ለ6 ዓመታት ያህል አገሪቷን አስተዳድረዋል።













