ሱዳን: ሕገወጥ ወርቅ ፈላጊዎች ጥንታዊ ቅርስ አወደሙ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሕገወጥ ወርቅ ፈላጊዎች 2000 ዓመት እድሜ እንዳለው የሚታመነውን የቅርስ ስፍራ ማውደማቸው ተገለፀ።
የሰሃራ በረሃ አካል በሆነው የሱዳን ምሥራቃዊ አካባቢ የሚገኘው ይህ የቅርስ ስፍራ ሙሉ በሙሉ መፈራረሱም ተገልጿል።
ጃባል ማራግሃ የሚሰኘው ይህ የቅርስ ስፍራ በታሪክና ቅርስ አጥኚዎች ዘንድ እድሜው ከክርስቶስ ልደት በፊት 350 ዓመት በፊት፤ እንዲሁም ከክርስቶስ ልደት በኋላ 350 ባሉት ዓመታት መካከል በነበረው የሜሮይቲክ ዘመን ውስጥ የተገነባ አነስተኛ መንደር እንደሆነ ይታመናል።
የሱዳን ቅርስና ሙዚየም ባለስልጣናት ባለፈው ወር ከዋና ከተማዋ 270 ኪሎ ሜትር የሚርቀውን ይህንን ታሪካዊ ስፍራ በጎበኙበት ወቅት ሁለት መቆፈሪያ ማሽኖችና አምስት ሰዎች በቁፋሮ ላይ ተሰማርተው ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ግለሰቦቹ 17 ሜትር ጥልቀትና 20 ሜትር ስፋት ያለው ጉድጓድ ቆፍረው ነበር ብለዋል።
ሃባብ እድሪስ አህመድ አርኪዮሎጂስት ሲሆኑ በተፈጠረው ነገር ደንግጠዋል። በስፍራው እአአ ከ1999 ጀምሮ እንደሰሩ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል በመናገር "እዚህ ስፍራ ቁፋሮ ሲያካሄዱ የነበሩ ሰዎች ያላቸው ዓላማ አንድ ብቻ ነው፤ ወርቅ መፈለግ። የሆነ የእብድ ሥራ ነው የሰሩት። በፍጥነት ወርቅ ለማግኘት ከባድ የቁፋሮ መሳርያ ተጠቅመዋል" ብለዋል።
ምንም እንኳ እንደ ግብጽ እጅጉን ስማቸው የገነነና በበርካቶች ዘንድ የሚታወቁ አይሁኑ እንጂ ሱዳን በመቶዎች የሚቆጠሩ ፒራሚዶችና ጥንታዊ ስፍራዎች የሚገኙባት አገር ናት።
የሱዳን አርኪዮሎጂስቶች እንዲህ ያለ ችግር አዲስ አለመሆኑን በመጥቀስ እያደገ የመጣ ነው ሲሉ አሳሳቢ መሆኑን ይገልጻሉ።
በአባይ ወንዝ ዳርቻ በሚገኘውና ሳይ በሚሰኘው ደሴት ላይ በፈርኦን ዘመን እንደነበሩ የሚታመኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመቃብር ስፍራዎች በመዝባሪዎች ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል።
"በሱዳን ከሚገኙ በሺዎች ከሚቆጠሩና በሚገባ ከሚታወቁ ታሪካዊ ስፍራዎች ቢያንስ ቢያንስ በመቶዎች የሚቆጠሩት ወድመዋል አልያም ፈርሰዋል" ይላሉ የሱዳን ቅርስና ሙዚየሞች ዳይሬክተሩ ሃተም አል ኑር።

የፎቶው ባለመብት, AFP
አክለውም ለቅርሶቹ የሚደረግ ጥበቃ አለመኖር ለዘራፊዎች በቀላሉ እንዲጋለጡ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
ሱዳን በአፍሪካ በወርቅ አምራችነት ከደቡብ አፍሪካና ከጋና በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ወርቅ ለአገሪቱ ባለፈው ዓመት 1.2 ቢሊየን ዶላር ያስገኘው በሕጋዊ መልኩ በማውጣት ለዓለም አቀፍ ገበያ የተሸጠው መሆኑን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ገልጿል።
አንዳንድ የአካባቢ ባለስልጣናትና ነጋዴዎች ለሕገወጥ ማዕድን አውጪዎች ማሽን በመስጠት እንደሚያበረታቷቸው ይነገራል።
የማዕድን ቆፋሪዎችም በቁጥጥር ስር በሚውሉበት ወቅት የሚጣልባቸው ቅጣት እምብዛም መሆኑ ግለሰቦቹ ከድርጊታቸው እንዳይታቀቡ ማድረጉን ይገልፃሉ።
የጃባል ማራግሃን ታሪካዊ ስፍራን ያወደሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ቢውሉም በነጻ መለቀቃቸው ተሰምቷል።
"በእስር መቆየት ነበረባቸው። ማሽናቸውም ቢሆን መያዝ ነበረበት። ሕጉ አለ" ብለዋል በሱዳን የቅርስ ክፍል ሰርተው የሚያውቁት መሃሙድ አል ታይብ።
እነዚህን የታሪክ ስፍራዎች በዘላቂነት ለመከላከል መፍትሄው ወጣቶችን ስለአገሪቱ ታሪክ ማስተማር መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ያኔ ታሪካቸውንና ቅርሳቸውን ይጠብቁታል ሲሉ የሚመክሩት ደግሞ ፕሮፌሰር ሃባብ ኢድሪስ ሙሃመድ ናቸው።














