ሊቢያ: ግብጽ ስለምን ጄነራል ሃፍታርን ለመደገፍ ጦሯን ወደ ሊቢያ ላከች?

እስቲ የጎረቤትዎ ቤት በእሳት እየነደደ ማንም እሳቱን ለማጥፋት የሚመጣ ሰው አልያም እሳት አጥፊ ቡድን ባይመጣና እሳቱ ወደ እርስዎ ቤትም ተዛምቶ ቤተሰብዎን ሲያቃጥል ያስቡት።

ግብጽ በሊቢያ እየሆነ ያለውን ነገር ከዚህ አይነት እሳት ለይታ አታየውም። ምክንያቱም የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊና በእርሳቸው የሚመራው መንግስታቸው በአውሮፓውያኑ 2011 ካበቃላቸው በኋላ አገሪቱ እንዳልነበረች ሆናለች።

በሊቢያ የሚታየው አለመረጋጋትና የሰላም እጦት ደግሞ ወደ ግብጽም እንዳይጋባ ስጋት አለ።

ሊቢያ እስካሁን ድረስ በአግባቡ ስራቸውን የሚሰሩ መስሪያ ቤቶችም ሆነ ማንኛውም አይነት የደህንነት እና ወታደራዊ አካላት የሌሏት ሲሆን 1100 ኪሎሜትር የሚሆነው ድንበሯም እየተጠበቀ አይደለም። በተጨማሪም አገሪቱ የጦር መሳሪያ ማከማቻ እየሆነች ነው።

ሊቢያ ችግር ውስጥ መግባት የጀመረችው ዜጎቿ እንዴት ወደፊት መጓዝ እንዳለባቸው መስማማት ሲያቅታቸውና አክራሪ ታጣቂዎች እስላማዊ ሊቢያን እንፈጥራለን ብለው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ነው።

በግብጽ 2013 ላይ እስላማዊው መሪ ፕሬዝደንት ሞሀመድ ሙርሲን ከስልጣን ከተባረሩ ወዲህ አገሪቱ የነዚህ ታጣቂዎች የመጀመሪያ ኢላማ ሆናለች።

  • 2104 ሰኔ ላይ ስድስት የግብጽ ድንበር ጠባቂዎች ተገደሉ
  • 2017 ላይ ደግሞ ጂሃዳዊ ቡድኖች ወደ ግብጽ ግዛት በመግባት 16 ወታደሮችን በመግደል ሌሎች 13 ወታደሮችን ደግሞ አቆሰሉ
  • እዛው ሊቢያ ውስጥ ግብጻውያን መምህራንም ኢላማ ሆነዋል። 2015 ላይ እስላማዊ ታጣቂዎች 21 ክርስቲያን ግብጻውያንን ካገቱ በኋላ ገድለዋቸዋል።

በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት በሊቢያ ጊዜያዊ መንግስት ለመመስረትና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት በተደጋጋሚ ተሞክሯል።

በሊቢያ በእስላማዊ ፅንፈኛ አክራሪዎች በተሞላው ምዕራባዊ ክፍል እና ጸረ ኢስላማዊ አቋም ያላቸው በምስራቅ በኩል ለስልጣን እየተሻኮቱ ሲሆን ግብጽም በዚህ ሰአት ጎራዋን እየለየች ነው።

የሙስሊም ወንድማማቾች ቡድንን አሸባሪ በማለት የፈረጀችው ግብጽ በሊቢያ ኢስላማዊ አቀንቃኞች ላይ ጦርነት ያወጁት ጀነራል ካሊፋ ሀፍታርን መደገፏ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ጀነራል ካሊፋ በስተምዕራብ በኩል ድጋፍ ያላቸው ታጣቂዎችን በመዋጋት ቤንጋዚን እና ሌሎች ትልልቅ ከተማዎችን እየተቆጣጠሩ ይገኛሉ።

ላለፉት ስድስት ዓመታት ደግሞ የግብጽ ዋናኛ አላማ በሊቢያ ያለውን እሳት በሊቢያ እንዲቆይና ወደ ድንበሯ እንዳይገባ ማድረግ ነው።

ለዚህም ነው ጀነራል ካሊፋ ሀፍታርን መደገፍ የመረጠችው።

ነገርግን ልክ በአካባቢው ትልቅ ተሰሚነትና ኃይል ያላት ቱርክ በሊቢያ የሚገኙ ኢስላማዊ ቡድኖችን መደገፍ ስትጀምር ነገሮች ወደ ሌላ አቅጣጫ መሄድ ጀምረዋል።

የጀነራል ካሊፋ ሀፍታርን ግስጋሴ ለማስቆምና ዋና ከተማዋ ትሪፖሊ በጀነራሉ ቁጥጥር ስር እንዳትወድቅ በማሰብ ቱርክ ቴክኒካዊና ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ ጀምራለች።

ከቱርክ በተደረገለት ድጋፍ በመነሳሳት ትሪፖሊ የሚገኘው አስተዳደር ወደ ጦርነት በመግባት ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችን ከጀራል ካሊፋ ሀፍታር ለማስለቀቅ ቆርጦ መነሳቱን አስታውቋል።

ቱርክ በሺዎች የሚቆጠሩ የሶሪያ ወታደሮችን እና ጂሃዳዊ ታጣቂዎችን ወደ ትሪፖሊ በማስገባት በጦርነቱ እንዲረዱ ማድረጓ ግብጽ ዝም ብላ ነገሮችን እንዳትመለከት አስገድዷታል።

ሰኔ ወር ላይ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በርካቶችን ያስደነቀ የግብጽ ወታደራዊ ትዕይንት ከታደሙ በኋላ አንድ ነግ ብለዋል።

''የግብጽና የሊቢያን ታሪካዊ ግንኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ግብጽ በሊቢያ እየሆነ ባለው ነገር ላይ ጣልቃ እንድትገባ በቂ ምክንያት አላት። ከውጭ አገራት የሚመጡ ተጽህኖዎችን በመቋቋም አገራዊ ጥቅሟንም ማስጠበቅ ግድ ይላታል'' ሲሉ ተደምጠዋል።

በሜዲትራኒያን ባህር እና ሰርጥ በኩል ማንኛውም አይነት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለግብጽ ሉአላዊነቷን እንደ መጣስ ነው የሚቆጠረው። ለትሪፖሊ ታማኝ የሆኑ ሚሊሻዎች በዚህ በኩል ለማቋረጥ የሚሞክሩ ከሆነ ግብጽ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እንደምትንቀሳቀስና ቀይ መስመር እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ካሉ ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ የግብጽ ፓርላማ ሃሳባቸውን ሙሉ በሙሉ ደግፎታል። የአገሪቱ መከላከያ ኃይሎች ዋና አዛዥ የሆኑት ፕሬዝዳንት አብዱልፋታህ አልሲሲ አስፈላጊ ነው ብለው ባመኑት አካባቢ ወታደሮችን እንዲኣዘምቱም ጭምር ፈቃድ አግኝተዋል።

መቀመጫውን ትሪፖሊ ያደረገው አስተዳደር ደግሞ ፕሬዝደንቱ ባስተላለፉት ወታደራዊ ማስፈራራት ደስተኛ እንዳልሆነና ጉዳዩን 'ጦርነት እንደማወጅ' እንደሚመለከው አስታውቋል።

የግብጽ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ፕሬዝዳንታቸውን በማሞካሸት የመከላከያ ሰረዊቱ ከዓለም ጠንካራ ከሚባሉት እንደሆነ በመግለጽ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ሌላው ቀርቶ የግብጽን ወታደራዊ ብቃት ከቱርክ ጋር በማነጻጸርም የግብጽን ጦር ሲያሞካሹ ነበር።

ነገር ግን አንዳንድ የአካባቢው ተንታኞችና ፖለቲከኞች ግብጽ ብሄራዊ ጥቅሜን አስጠብቃለው በማለት በምታደርገው እንቅስቃሴ መሀል በሊቢያ እሳት ውስጥ ገብታ ያልታሰበ ጉዳትና ኪሳራ እንዳያጋጥማት እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።

በተጨማሪም ተንንታኞቹ የግብጽ ወታደሮች ከእስራኤል ጋር ከተዋጉበት የአውሮፓውያኑ 1973 ጦርነት ወዲህ እዚህ ግባ የሚባል የጦርነት ልምድ አለመኖሩ ነገሮችን ከባድ ሊያደርግባቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።

ስለዚህ ግብጽ ያሏት ሁለት አማራጮች አሉ።

አንደኛው ጁፍራ እና ሰርጥ ላይ ሊፈጸሙ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመከላከል ቀደም ብላ እርምጃ መውሰድ ሲሆን ይህ እርምጃ ግን ጦርነት ሊቀሰቅስ የሚችልበት እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል።

ሁለተኛው አማራጭ ማንኛውም አይነት ቡድን ግብጽ ያስቀመጠችውን ቀይ መስመር እስከሚያልፍ ድረስ መጠበቅ ነው። ይሄኛውም አማራጭ ቢሆን ግን ከዘገየ በኋላ ሊወሰድ የሚችል እርምጃ በመሆኑ ለራሷ ግብጽና ሊቢያ ላሉ ወዳጆቿ አስጊ ነው።

ወጣም ወረደ ግብጽ ሊቢያን በተመለከተ ግራ የሚያጋባ አጣብቂኝ ውስጥ የወደቀች ትመስላለች።