ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግብጽ በሊቢያ ውስጥ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት ቱርክ ተቃወመች
የቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ሊቢያ ውስጥ እተካሄደ ባለው ግጭት የግብጽን ጣልቃ አጥብቀው ኮነኑ።
ኤርዶዋን ካይሮ በሊቢያ ግጭት ውስጥ ጀነራል ካሊፍ ሃፍታርን መደገፏ ሕገ-ወጥ ተግባር ነው ሲሉ ወንጅለዋል።
በአሁኑ ወቅት ሊቢያ ውስት በሚካሄደው ግጭት ሁለት ዋነኛ ተቀናቃኝ ኃይሎች የሚገኙ ሲሆን አንደኛው በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠውና መቀመጫውን በትሪፖሊ ያደረገው በጠቅላይ ሚንስትር ፋዬዝ አል-ሴራጅ የሚመራው መንግሥት ነው ።
ሌላኛው ደግሞ መቀመጫውን በምሥራቅ ሊቢያ ቶብሩክ እና ቤንጋዚ ከተሞች ያደረገውን በጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራው አማጺ ኃይል ነው።
ጀነራል ሃፍታር "እስላማዊ አሸባሪዎችን" እዋጋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ዮርዳኖስ ጽንፈኞች ከቀጠናው መጽዳት አለባቸው በማለት አጋርነታቸውን ከጀነራሉ ጋር አድርገዋል።
ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በሩሲያ መንግሥት ተከፋይ የሆኑ የሌሎች አገራት ቅጥረኛ ወታደሮች ከጀነራሉ ጎን ሆነው ይዋጉ ነበር። የክሬምሊን መንግሥት ግን ቀጥተኛ ተሳትፎ የለኝም ይሏል።
በሌላኛው በኩል ደግሞ ቱርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና የያለውን መንግሥት ትደግፋለች። ኤርዶዋን በሊቢያ በእጅ አዙር ጦርነት በተፋፋመው የእርስ በእስር ጦርነት 'ጨዋታ' ቀያሪ ናቸው ይባላሉ።
ለዚህም ምክንያት ኤርዱዋን ጦራቸውን ወደ ትሪፖሊ ካዘመቱ በኋላ በተመድ እውቅና ያለው መንግሥት በትሪፖሊ አቅራቢያ በነበሩ የጀነራሉ ጦር አባላት ላይ ድልን መቀናጀቱ ነው።
ከመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ውሰጥ ተገልላ የምትገኘው ኳታር፤ በሊቢያ ጉዳይ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከቱርክ ጎን ተሰልፋለች።
ጦራችን በሊቢያ ያለውን ሁኔታ መቀየር ይችላል
የግብጹ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሰ ትናንት የአገራቸው ጦር በሊቢያ ያለውን ሁኔታ በፍጥነት እና በማያወላውል ሁኔታ የመቀየር አቅም እንዳለው መናገራቸው ተዘግቧል።
ኤርዶዋን ግብጽ በሊቢያ ያላትን ተሳትፎ የኮነኑት የካይሮ መንግሥት ጦሩን ወደ ሊቢያ ላዘምት እችላለሁ የሚል ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ተከትሎ ነው።
የቱርኩ ቴሌቪዝን በበኩሉ ኤርዶዋን "በግብጽ የተወሰዱት እርምጃዎች በተለይ ደግሞ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ከሞከረው ሃፍታር ጋር መወገናቸው ሕገ-ወጥ መሆናቸውን ያሳያል" ማለታቸውን ዘግቧል።