ሱዳናውያን ጥብቅ የእስልምና ሕግጋት መሻሻል የለባቸውም ሲሉ ለተቃውሞ ወጡ

በቅርቡ በአንዳንድ ጥብቅ እስላማዊ ሕጎቿ ላይ ማሻሻያዎችን ያደረጉት የሱዳን ባለስልጣናት ተቃውሞ ገጠማቸው።

በርካታ የሸሪአ ሕግጋት ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚፈግፉ ሱዳናውያን በቀርቡ የአገሪቱ የሽግግር መንግሥት ጥብቅ የእስልምና ሕግጋትን ማሻሻሉን ተቃውመው አደባባይ ወጥተዋል።

በቅርቡ የሱዳን መንግሥት ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች የአልኮል መጠጥ እንዲጠጡ ከመፍቀዱ በተጨማሪ ሐይማኖት የመቀየር መብትን ጨምሮ በርካታ ለውጦችን ይፋ አድርጎ ነበር።

የሱዳን ፍትህ ሚንስቴር ባለስልጣናት ሰዎች ለፈጸሙት 'ኢ-ሞራላዊ ተግባር' በአደባባይ እንዲገረፉ የሚያዘው ትዕዛዝ እንዲቆም መታወጁንም ተናግረው ነበር።

ትናንት ከአርብ ጸሎት በኋላ ግን መንግሥት ያስተዋወቀውን ማሻሻያዎች ለመቃወም የወጡ ሰልፈኞች፤ "የፈጣሪ ሕግ መቀየር የለበትም" እንዲሁም "መንግሥት በሐይማኖት ጣልቃ መግባት የለበትም" የሚሉ መፈክሮችን ይዘው መውጣቻቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ተቃዋሚዎቹ የሱዳን የሽግግር መንግሥት መሪ የሆኑትን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክን በስም እየጠሩ "ሃምዶክ፤ ካርቱም ኒው ዮርክ አይደለችም" ሲሉም ተደምጠዋል።

የሽግግር መንግሥቱ ያሻሻላቸው ሕጎች የትኞቹ ናቸው?

በተሻሻለው ሕግ መሠረት ከአሁን በኋላ ሱዳናውያን ሴቶች ጉዞ ለማድረግ ከወንድ የቤተሰብ አባል ፍቃድ ማግኘት አይጠበቅባቸውም።

ከዚህ ቀደም በሱዳን የአልኮል መጠጥ መጠጣት አይፈቀድም ነበር። አሁን ግን ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች አልኮል በቤታቸው መጠቀም ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ሙስሊሞች ባሉበት ቦታ አልኮል ሲጠጡ ቢገኙ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተነግሯል። የእስልምና እምነት ተከታዮች ግን አሁንም ቢሆን አልኮል መጠጣት አይፈቀድላቸውም ሲሉ የፍትህ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

ሙስሊም ያለሆኑ ግሰቦች አልኮል ከመጠቀም ባሻገር፤ መሽጥ እና ከውጪ ማስገባት ይችላሉ ተብሏል። የሱዳን መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰኩት 3 በመቶ የሚሆኑ ሙስሊም ያልሆኑ ሱዳናውያንን መብትን ለመጠበቅ ነው ብሏል።

በሱዳን እስካሁን ድረስ የእስልምን ሐይማኖትን የሚቀይሩ ሰዎች የሞት ቅጣትን ጨምሮ ከባድ ቅጣት ይጣልባቸው ነበር። የሽግግር መንግሥቱ ሰዎች ሐይማኖታቸውን የመቀየር መብት አላቸው ሲል ደንግጓል።