ትራምፕ ዜጎቻቸው ጨምብል እንዲያደርጉ አላስገድድም አሉ

የአሜሪካው ፕሬዝዳናት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት ዜጎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልን እንዲያደርጉ እንደማያዙ አስታወቁ።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት የአገሪቱ የተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አንተኒ ፋውቺ የግዛቶችና የአካባቢ አስተዳዳሪዎች ሕዝቡ የፊት እና አፍ መሸፈኛ ጭምብል እንዲጠቀም በተቻለ አቅም "እንዲያስገድዱ" መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።

ዶክተር ፋውቺ እንዳሉት የፊትና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ በሽታውን ለመከላከል "በጣም አስፈላጊ ስለሆነ፤ ሁላችንም ልንጠቀምበት ይገባል።"

በአሜሪካ ጭምብል የመጠቀም ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ የፖለቲካዊ ውዝግብ ምንጭ ከሆነ ወራት ተቆጥረዋል።

ነገር ግን በአገሪቱ ያሉ የአብዛኞቹ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች ማንኛውም ሰው ከቤቱ ውጪ በሚሆንበት ጊዜ ጭምብል ማድረግን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ አድርገውታል።

ለረጅም ጊዜ ጭምብል ማድረግን ሲቃወሙ የነበሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ጭምብል አድርገው ታይተዋል።

ነገር ግን ትናንት አርብ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልን መጠቀም ግዴታ መደረግን እንደማይስማሙበት "ሕዝቡ ነጻነት ሊሰጠው ይገባል" በማለት አመልክተው።

ከቀናት በፊት የአሜሪካ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም የሆነው የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ባወጣው መግለጫ ላይ ሕዝቡ ጭምብል እንዲጠቀም አጥብቆ ጠይቋል።

"የኮሮናቫይረስን የምነከላከልበት ዘዴ አለን" ያሉት የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶክተር ሮበርት ሬድፊልድ ናቸው። "ከጨርቅ የሚሰሩ ጭምብሎች የቫይረሱን መስፋፋት ለማስቆምና ለመቀነስ ዋነኛ ዘዴ ነው። በተለይ ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች ላይ መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

በደቡባዊ አሜሪካ የምትገኘው የጆርጂያ ግዛት ገዢ ብሪያን ኬምፕ የአፍን የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግን ሲቃወሙ የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን ነዋሪዎች እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።

በግዛቲቱ የምትገኘው የአትላንታ ከተማ ከንቲባ ኬይሻ ላንስ ቦቶምስ የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን ቀደም ብለው ከንቲባዋ በከተማዋ ውስጥ ጭምብል ማድረግ ግዴታ መሆኑን በማወጃቸው ከአገረ ገዢው ኬምፕ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።