የሊቢያ የእርስ በእርስ ጦርነት፡ የሌሎች ሃገራት ጣልቃ ገብነት

የሊቢያ ጉዳይ የዓለም ትኩረትን እንደሳበ ነው። በብዙ ፍላጎት የተወጠሩ የሊቢያ ኃይሎች እና ሌሎች ሃገራት ሊቢያን ሰላም ነስተዋታል።

በአሁኑ ሰዓት በሊቢያ ሁለት ዋነኛ ተቀናቃኝ ኃይሎች ይገኛሉ። በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠው በጠቅላይ ሚንስትር ፋዬዝ አል-ሴራጅ የሚመራው መንግሥት እና በጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራው አማጺ ኃይል ናቸው።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ እውቅና ባለው መንግሥት እና በአማጺያኑ መካከል በነበረ ግጭት ቢያንስ 2 ሺህ ሊቢያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። 146ሺህ የሚሆኑት የመኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።

አሁን ላይ ሁለቱ ኃይሎች በቱርክ እና ሩሲያ ጫና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ይሁን እንጂ የተኩስ አቁሙን ስምምነት ለመፈረም ሲያመነቱ የቆዩት ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር ስምምነቱን ሊጥሱት ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።

ሊቢያውያን በሙዓመር ጋዳፊ አምባገነናዊ ሥርዓት ሥር ሳሉ፤ ይክፋም ይልማም የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ነበሩ። ነጻ ትምህርት እና ነጻ የህክምና አገልግሎት አይለያቸውም ነበር። ዛሬ ላይ አምባገነኑ ሙዓመር ጋዳፊ ከሥልጣን ከተባረሩ 9 ዓመታት በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሊቢያውያን ሰላም ናፍቋቸዋል። የዳቦ ዋጋ ተወዶባቸዋል።

ለመሆኑ ሊቢያውያን እዚህ አጣብቂኝውስብስ ነገር ውስጥ እንዴት ገቡ?

ልክ እንደ ሶሪያ ሁሉ፤ የሊቢያውያን ሰቆቃ የጀመረው የአርብ አብዮቱን ተከትሎ ነው።

እአአ 2011 ላይ በምዕራባውያኑ ኔቶ (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት) ድጋፍ የረዥም ጊዜ የሊቢያ መሪ የነበሩት ሙዓመር ጋዳፊ ከሥልጣን ተባረሩ።

አምባገነኑ ሙዓመር ጋዳፊ በሊቢያውያን ለውጥ ናፋቂ ወጣቶች መንገድ ላይ ተጎተቱ፤ አይደፈሬው ተዋረዱ፤ ከዚያም በጥይት ተመትተው ተገደሉ። በሊቢያ አዲስ ለውጥ መጣ ተባለ።

ሊቢያውያን ግን አምባገነናዊ ሥርዓቱን በሕዝባዊ አብዮት ሲገረስሱት፤ ነጻነትን እና የተሻለ ሥርዓትን አልመው ነበር።

የሙዓመር ጋዳፊ ሞት ግን ሊቢያውያን የተመኙትን ለውጥ ሳይሆን፤ መግቢያ መውጫ ያሳጣቸውን የእርስ በእርስ ጦርነት ነው ያስከተለው።

የተባበሩት መንግሥታት በጠቅላይ ሚንስትር ሰርጀ የሚመራ መንግሥት መቀመጫውን በትሪፖሊ እንዲያደርግ አመቻቸ።

ሁሉም በዚህ አልተስማማም፤ ጀነራል ሃፍታ ሥልጣን ፈለጉ።

ጀነራሉ በምስራቅ ሊቢያ በሚገኙ ቶበሩክ እና ቤንጋዚ ከተሞች መቀመጫቸውን አድርገው የራሳቸውን ጦር አደራጁ። ተጽእኖ ፈጣሪው ጀነራል፤ የሊቢያ ብሔራዊ ጦር የተሰኘ ኃይል አቋቁመው ካለ እኔ ለሊቢያ የሚፈይድ የለም፤ እኔ እንጂ ማንም "እስላማዊ አሸባሪዎችን" አያስወግድም አሉ።

ከዚያም በተመድ እውቅና ያለውን መንግሥት መውጋት ተያያዙት። ትሪፖሊን ለመቆጣጠር የጦር እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ 9 ወራት ተቆጠሩ።

ከጀነራሉ ጦር በተጨማሪ በሊቢያ ''ነጻ'' አውጪ ነን የሚሉ ኃይሎች በርካቶች ናቸው። ከየመሸጉበት እየወጡ፤ አንዱ አንዱን ይወጋል። በሊቢያ ''እስላማዊ መንግሥት'' መመሠረት አለበት ብለው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም ብዙ ናቸው።

የእጅ አዙር ጦርነት

በሊቢያ የሚንቀሳቀሱት ኃይሎች የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የሌሎች የውጪ ሃገራት ፍላጎትን ለማሳካት ነፍጥ አንግበዋል።

በቀጠናው የሚገኙ ሃገራት በተለያየ አሰላለፍ የእጅ አዙር ጦርነት ወይም የውክልና ጦርነት ያካሂዳሉ።

ጀነራል ሃፍታር "እስላማዊ አሸባሪዎችን" እዋጋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ጆርዳን ጽንፈኞች ከቀጠናው መጽዳት አለባቸው በማለት አጋርነታቸውን ከጀነራሉ ጋር አድርገዋል።

ጆርዳን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ከድጋፍም አልፈው የጀነራሉን ጦር አስታጥቀዋል፤ በተመድ እውቅና ባለው መንግሥት ላይ ጥቃት ሲሰነዘር የአየር ላይ ድጋፍ ያደርጋሉ።

በግጭቱ ወቅት የተገደሉት ንጹሃን ዜጎች ለሞት ያበቃቸው የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ጦር መሳሪያ ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት ይከሳል።

ከእነዚህ ሃገራት በተጨማሪ፤ ጎረቤት ሃገር ግብጽም የጀነራሉ አጋር ነች። አል ሲሲ ለጀነራል ሃፍታር ጦር የሎጂስቲክ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛሉ።

ከአካባቢው ሃገራት በተጨማሪም ሞስኮ በሊቢያ እጇን እያስገባች እንደሆነ እየተነገረ ነው። ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በሩሲያ መንግሥት ተከፋይ የሆኑ የሌሎች ሃገራት ወታደሮች ከጀነራሉ ጎን ሆነው እየተዋጉ ይገኛሉ። የክሬምሊን መንግሥት ግን ቀጥተኛ ተሳትፎ የለኝም ይላል።

በሌላኛው በኩል ደግሞ ቱርክ የተመድ እውቅና የተሰጠውን መንግሥት ትደግፋለች።

ከጥቂት ቀናት በፊትም ቱርክ ወደ ሊቢያ የትሪፖሊን መንግሥት ለመደገፍ ጦሯን ልካለች።

የቱርክ መንግሥት ጦሩን ወደ ሊቢያ የላከው "የሥልጠና እና የምክር አገልግሎት" ለመስጠት ታስቦ ነው ብሏል።

በሊቢያ መንግሥት ውስጥ የሚገኝ የቢቢሲ ውስጥ አዋቂ ግን በቱርክ በኩል ወደ ሊቢያ ከመጡ ወታደሮች መካከል በቱርክ የሚደገፉ የሶሪያ አማጺያን ይገኙበታል ብሏል።

በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ውስጥ ብዙውን ግዜ ተገልላ የምትገኘው ኳታር፤ በሊቢያ ጉዳይ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከቱርክ ጎን ተሰልፋለች።

የምዕራባውያን ሃገራት ፍላጎቶች

ሌላ የሊቢያ ጉዳይ ያገባኛል የምትለው ፈረንሳይ፤ የቱርክን አሰላለፍ ተቀላቅላለች። ፈረንሳይ የተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለውን መንግሥት እደግፋለሁ ትበል እንጂ ልቧ ያለው ከጀነራሉ ጦር ጋር ነው ተብሎ ይታመናል።

የቀድሞ የሊቢያ ቅኝ ገዢ የሆነችው ጣሊያን፤ ፓሪስ ለጀነራሉ ጦር የምታደርገውን ድጋፍ አጥብቃ ካወገዘች በኋላ፤ ሮም ሁልጊዜም ተመድ እውቅና ለሰጠው መንግሥት ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል አስታውቃለች።

በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች በሊቢያ በኩል አድርገው ሜደትራኒያን ካቋረጡ በኋላ የመጀመሪያው መዳረሻቸው ጣሊያን ነች። በዚህም ጣሊያን የስደተኞችን ፍሰት ለማስቆም በሊቢያ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አለብኝ ባይ ነች።

ኃያሏ ሃገር አሜሪካም በሊቢያ በቀጥታ እጇን አስገብታለች። በደቡብ ምዕራብ ሊቢያ የሚገኙ የአይኤስ ሚሊሻዎች ላይ እርምጃ ትወስዳለች።

ይህ ሁሉ ሃገር በሊቢያ ጉዳይ እጁን የሚያስገባው ለምን ይሆን?

በሊቢያ የእርስ በእርስ ጦርነት እጃቸውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያስገቡት ሃገራት ቁጥር ከፍተኛ ነው።

ለዚህም የመጀመሪያው ምክንያት ሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያላት ሃገር ነች። በተፈጥሯዊ ጋዝ ገበያ ላይም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሃገር መሆን ትችላለች።

ሌላኛው ምክንያት መዳረሻቸውን አውሮፓ ለማድረግ ከአፍሪካ የሚሰደዱ ወጣቶች መነሻቸውን የሚያደርጉት ከሊቢያ ነው። ሊቢያ ከ2ሺህ ኪ.ሜትር በላይ ከሜድትራኒያን ባህር ጋር እንደምትዋሰን እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።

ከኢራቅ እና ሶሪያ ድል የተመታው ጽንፈኛው አይኤስ በሊቢያ በረሃዎች ላይ እግሩን እየከተተ መሆኑ ተነግሯል። ይህ ለሊቢያ እና ጎረቤት አገሮች ብቻ ሳይሆን ለዓለም ደህንነት ስጋት ነው።