ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጃፓናዊው ቢሊዬነር ወደ ጨረቃ አብራው የምትጓዝ 'ውሃ አጣጭ' እየፈለገ ነው
ጃፓናዊው ቢሊዬነር ዩሳኩ ማይዛዋ በስፔስ ኤክስ መንኩራኩር ወደ ጨረቃ አብራው የምትጓዝ ሴት ጓደኛ እየፈለገ እንደሆነ አሳውቋል።
በፋሽን ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማራው የ44 ዓመቱ ዩሳኩ ወደ ጨረቃ የሚጓዝ የመጀመሪያው ሲቪል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ጉዞው የዛሬ ሁለት ዓመት በግሪጎሪ አቆጣጠር 2023 ላይ የሚከናውን ሲሆን ከ1972 በኋላ ወደ ጨረቃ የሚደረግ የመጀመሪያው ጉዞ ሊሆን ይችላል።
በመረጃ መረብ አማካይነት ፍላጎቱን ይፋ ያደረገው ጎልማሳው ቱጃር ይህንን 'ልዩ ጉዞ' አብራኝ የምትጓዝ ልዩ እንስት ከወዴት አለች? እያለ ነው።
ከ27 ዓመቷ ተዋናይት ፍቅረኛው ጋር በቅርቡ የተለያየው ዩሳኩ በድረ-ገፁ ላይ ባለ መረጃ መስበስበያ ላይ ሴቶች መስፈርታቸውን እንዲያስቀምጡ አቤት ብሏል።
«ብቸኝነትና ባዶነት ሊጠናወቱኝ እየሻቱ ስለሆነ መፍትሄው አንዲት ሴትን ማፍቀር ነው» ሲል በድረ-ገፁ አሥፍሯል። «የሕይወት አጋር እፈልጋለሁ፤ ከወደፈቷ አጋሬ ጋር ከውጭው ምህዋር ሆኜ የዓለም ሰላምን እሰብካለሁ» ሲል አክሏል።
ሶስት ወራት የሚቆይ የዩሳኩ ውሃ አጣጭ ፍለጋ ሂደት ብዙ መስፈርቶችን አዝሎ በድረ-ገፁ ላይ ሰፍሯል።
በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ያልሆነች፣ ዕድሜዋ ከ20 በላይ፣ ቅን አስተሳሰብ ያላትና ወደ ሕዋ ለመብረር ዝግጁ የሆነች የዩሳኩ መስፈርቶች ናቸው።
የማመልካቻው ቀን መዝጊያ ጥር 8/2012 ሲሆን አሸናፊዋ ሴት በመጋቢት ወር መጨረሻ ይፋ ትሆናለች።
አንድ ባንድ ውስጥ በከበሮ መቺነት ያገለግል የነበረው ዩሳኩ ወጣ ባሉ ድርጊቶቹ ይታወቃል። በዚህ ወር መጀመሪያ እንኳ በትዊተር ገፁ ላይ የሚሰፍሩ መልዕክቶቹን ለሌሎች ያጋሩ 100 ሰዎችን መርጬ 925 ሺህ ዶላር አከፋፍላለሁ ማለቱ አነጋጋሪ ነበር።
ዞዞ የተባለ የልብ ዲዛይን ባለቤት የሆነው ዩሳኩ የተጣራ ትርፉ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ይገመታል።