ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር፡ ወታደሮቻቸው ትሪፖሊን እንዲቆጣጠሩ አዘዙ

ሊቢያዊው የጦር ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር ወታደሮቻቸው የሊቢያን መዲና ትሪፖሊን በቁጥጥራቸው ሥር እንዲያውሉ አዘዙ።

ተጽእኖ ፈጣሪው የጦር ጀነራል ይህን መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው ነው።

ጀነራሉ ከዚህ ቀደም በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ይህን መሰል መልዕክት አስተላልፈው አያውቁም ተብሏል።

የጀነራል ሃፍታር መልዕክት በትሪፖሊ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል።

ጀነራሉ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ባለው መንግሥት ሥር የምትተዳደረውን ትሪፖሊን ለመቆጣጠር ከወራት በፊት የጦር እርምጃ ሲወስዱ ነበር።

ትሪፖሊን የሚያስተዳድረው መንግሥት ግን የጀነራል ሃፍታር ወታደሮች ትሪፖሊን እንዳይቆጣጠሩ የመከላከል እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል።

በተለይ በደቡባዊ ወደ ትሪፖሊ በሚወስዱ አቅጣጫዎች ላይ የጀነራሉ ወታደሮች ብዙ ሽንፈቶችን ተከናንበዋል።

የፖለቲካ ተንታኞች የአሁኑ የጀነራሉ መልዕክት ጦራቸው ሙሉ ኃይሉን ተጠቅሞ መዲናዋን ለመያዝ መወሰኑን ያመላክታል ብለዋል።

ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር ማናቸው?

ፊልድ ማርሻል ካሊፍ ቤልቃሲም ሃፍታር የአሜሪካ እና የሊቢያ ጥምር ዜግነት ያላቸው የሊቢያ ብሔራዊ ጦር የመሰረቱ እና የሚመሩ ተጽእኖ ፈጣሪ የጦር አለቃ ናቸው።

ጀነራል ካሊፍ የሊቢያ መንግሥት ከሚቀናቀኑ ሁለት ቡድኖች መካከል ከአንደኛው ጋር ጥምረት በመመስረት የትጥቅ ትግል ላይ ይገኛሉ። ጀነራሉ ከወራት በፊት ''አሸባሪዎች እና ወንጀለኛ ቡድኖች'' ባሏቸው አካላት ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል።

በጦር አዛዡ ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራው ጦር ከወራት በፊት በወሰደው እርምጃ በነዳጅ ሃብታቸው የበለጸጉ ደቡባዊ የሊቢያ ክፍሎች ተቆጣጥሯል።

በሊቢያ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ብዙ ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸውን ያጣሉ። በተለይ ደግሞ በመንግሥት ተቋማት እና በእስር ቤቶች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች የተገደሉ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለው መንግሥት በተደጋጋሚ ለሚፈጸሙት ጥቃቶች በጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራውን ቡድን ተጠያቂ ያደርጋል።

ሊቢያ ከ8 ዓመታት በፊት በቀድሞ መሪዋ ሙአመር ጋዳፊ ላይ ተቃውሞ ከተነሳ እና ከተገደሉ በኋላ ሰላም እና መረጋጋት እርቋት ቆይቷል።