የ16 ዓመቷ ግሬታ ተንበርግና ፕሬዝዳንት ትራምፕ እልህ ተጋብተዋል

የዓየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቿ ግሬታ ተንበርግ እና የዓለም ሀገራት መሪዎች እልህ ሲጋቡ የመጀመሪያቸው አይደለም። ግሬታ ከብራዚሉ ፕሬዝዳንት እስከ አሜሪካው ትራምፕ ድረስ ያላናደደችው የለም።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግሬታ በታይም መጽሔት የ2019 ዓ.ም "የዓመቱ ሰው" የሚለውን ስያሜ በማግኘቷ ብስጭት ብለዋል። ብስጭታቸውን ለመግለጽም ወደ ትዊተር ገጻቸው አምርተው አሸሙረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ግሬታን ጠቅሰው "ንዴቷን የመቆጣጠር ችግር አለባት" ሲሉ መልዕክት ካስቀመጡ በኋላ ቀጥለውም "... እናም ልክ እንደ ቀድሞ ጊዜ ሁሉ ከጓደኛዋ ጋር ወደ ሲኒማ ቤት መሄድ አለባት" ብለዋል። ከዚያም " ግሬታ ዘና በይ ዘና" ብለዋል።

ደግሞ ለትዊተር ማን ይሰንፋል ይመስላል የግሬታ መልስ። ሞባይሏን አንስታ የትዊተር ገጿን በመክፈት ትራምፕን ተቀበል ብላለች።

" አንዲት ታዳጊ ንዴቷን ለመቆጣጠር እየሰራች ነው። በአሁኑ ሰዓት የቆየ ፊልም ከጓደኛዋ ጋር እያየች ትገኛለች" ስትል የመልስ ምት አስፍራለች።

የ16 ዓመቷ ስውዲናዊ የዓለም የአየር ጠባይ ለውጥን በመቃወም የሚካሄደውን ዘመቻ ከመራች በኋላ በታይም መጽሔት የዓመቱ ሰው የተባለችው ረቡዕ ዕለት ነበር።

ግሬታ የፕሬዝዳንት ትራምፕንና የሌሎች ፕሬዝዳንቶች ትችት ለመመከት የትዊተር መልዕክቷን ስታሰፍር ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።

ሐሙስ ዕለት ግሬታ ትዊተር ገጿ ላይ "pirralha" የሚል የፖርቹጋል ቃል አስፍራ ነበር። ይህ ቃል ወዙ በተመጠጠ ትርጉም "ሁሉን ለኔ ባይ" ማለት ነው፤ ወይንም በሰው ገንዘብ የሚያለቅስ ህፃን በሉት።

ይህንን ቃል ያሰፈረችው ታዲያ ከብራዚሉ ፕሬዛዳንት ወስዳ ነው። የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ግሬታ በብራዚላ ቀደምት ሕዝቦች ላይ አስተያየቷን ከሰጠች በኋላ

" ግሬታ ኢንዲያናዎች አማዞንን ጥቅጥቅ ደን ከእሳት ለማዳን ሲታገሉ ተሰውተዋል በማለቷ የመገናኛ ብዙኀን ለዚህች ትንሽ 'ሁሉን ለኔ ባይ' ለሆነች ልጅ ትኩረት መስጠታቸው ይገርማል" ብለዋል ነበር ለጋዜጠኞች።

ግሬታ የትዊተር ጦርነቱ ላይ በጥቅምት ወርም ተገኝታ " ደግ ግን በቂ መረጃ የሌላት ታዳጊ" የሚል መልዕክት አስፍራ ነበር።

ይህ ደግሞ የሞስኮው ፕሬዝዳንት ፑቲን በሀገራቸው በተካሄደው ጉባኤ ላይ እርሷን የገለፁበት ነበር።

መስከረም ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ ተቆጥታ ስትናገር የሚያሳየውን ቪዲዮ ለጥፈው " ወደፊት ብሩህ እና መልካም ጊዜን የምትጠብቅ ደስተኛ ታዳጊ ትመስላለች' ብለው ተሳልቀዋል።

እርሷም ማን ከማን ያንሳል በሚል " ወደፊት ብሩህ ጊዜን የምትጠብቅ ደስተኛ ታዳጊ" የሚል መልዕክትን በትዊተሯ ላይ አስፍራለች።