ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይጄሪያ ለአፍሪካዊያን በሯን ክፍት ልታደርግ ነው
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ዜጎች ናይጄሪያ ለመግባት ለቪዛ ቀደም ብለው ማመልከትና ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸው ነበር።
ከአዲስ የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ግን ይህ ጣጣ ይቀራል። ዜጎችም በቀጥታ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ቪዛ ይታደላቸዋል ተብሏል።
ርዕሰ ብሔር መሐመድ ቡሃሪ እንደተናገሩት አፍሪካዊያን በአፍሪካ ውስጥ ነጻ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
የቡሃሪ ተቺዎች ግን ፕሬዝዳንቱ እንዲያውም ጸረ ፓን አፍሪካን ናቸው ይሏቸዋል።
ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ የናይጄሪያን ድንበር ቁጥጥር ማጥበቃቸውንና ይህም ንግድ ከአጎራባች አገሮች ጋር ለማድረግ ፈታኝ ማድረጉን ያወሳሉ።
ቡሃሪ በበኩላቸው ይህን ያደረኩት ሕገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ስል ነው ይላሉ።
ናይጄሪያ የመዳረሻ ቪዛን ተግባራዊ ስታደርግ ቪዛ አመልካቾች በአገራቸው ሳሉ የመግቢያ ቪዛ የማመልከት ሂደት ሙሉ በሙሉ ያስቀርላቸዋል።
በአዲሱ ዓመት ማንኛውም ከአፍሪካ አገራት የሚመጣ ዜጋ ናይጄሪያን እንደረገጠ ቪዛ ያገኛል።
ባለፈው ወር በአፍሪካ ባንክ በተደረገ አንድ ጥናት አፍሪካዊያን 49 ከመቶ በሚሆኑ የአፍሪካ አገራት ለመግባት ቪዛ የግድ ይላቸዋል። የመዳረሻ ቪዛን የሚያድሉ አገራት 26 ከመቶዎቹ ብቻ ናቸው። ምንም ቪዛ የማይጠይቁት ደግሞ 25 ከመቶዎቹ ብቻ ናቸው።
ከ54ቱ የአፍሪካ አገራት አጅግ ቀላል የቪዛ ጣጣ ያለባቸው አገራት ሲሸልስ፣ ቤኒን፣ ሴኔጋል፣ ሩዋንዳና ጋና ናቸው።
የቪዛ ሂደታቸው ፈታኝ የሚባሉት አገራት ደግሞ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ሊቢያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ጎረቤት ኤርትራ ናቸው።
ኢትዮጵያ የቪዛ ጣጣቸው ከበዙ አገራት ውስጥ ዋነኛ ተጠቃሽ እንደነበረች ሪፖርቱ ይጠቅሳል። ባለፈው ዓመት ግን የመዳረሻ ቪዛን ተግባራዊ በማድረጓ ቪዛን ካከበዱት አገራት ጎራ ተላቃለች።