"ልዩነቶች ተፈትተዋል. . . አቶ ለማ በሥራ ላይ ናቸው" አቶ ሳዳት

አቶ ለማ መገርሳ ከዚህ ቀደም ከብልጽግና ፓርቲ አመሠራረት ጋር ተያይዞ የነበራቸውን ልዩነት በፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ በኩል በተደረገው ውይይት ተፈቷል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ የከተሞች ፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ሳዳት ናሻ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትርና የቀድሞው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ፤ በኢሕአዴግ ውህደት እና በጠቅላይ ሚንስትሩ የመደመር ፍልስፍና እንደማያምኑ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መግለጻቸው ይታወሳል።

በወቅቱ "መዋሀዱ ትክክል አይደለም። ከሆነም በችኮላ መሆን የለበትም፤ ወቅቱም አይደለም" ያሉት አቶ ለማ፤ በመደመር ፍልስፍናም እንደማይስማሙ ከራድዮ ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቆይታ መናገራቸው ይታወቃል።

መከላከያ ሚንስትሩ ለአሜሪካ ድምጽ ይህን ካሉ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አቶ ለማ፤ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር አብረው ለውጡን እንደሚያስቀጥሉ ተነግሯል። ጠቅላይ ሚንስትሩ እና መከላከያ ሚንስትሩ በተፈጠረው ልዩነት ዙሪያ ቁጭ ብለው መወያየታቸውንና ተፈጥሮ የነበረው የሐሳብ ልዩነት ላይ መግባባት እንደቻሉና አብረው ለመስራት መስማማታቸው ተገልጿል።

ሁለቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የነበሯቸው ልዩነት በምን መልኩ ፈቱት? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ባያገኝም፤ አቶ ሳዳት ግን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ባደረገው ውይይት ልዩነቶችን ቀርፏል ብለዋል።

አቶ ሳዳት መከላከያ ሚንስትሩ በሥራ ላይ ነው የሚገኙት ያሉ ሲሆን፤ ልዩነት ተፈጥሮ የነበረው ካለመግባባት እንጂ መሠረታዊ የፖለቲካ አቋም ልዩነት ኖሮ አይደለም ብለዋል።

አቶ ለማ ለምን ዝምታን መረጡ?

አቶ ለማ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በጉዳዩ ላይ የአቋም ለውጦች ሲኖራቸው ለመገናኛ ብዙኃን ወጥተው እንደሚናገሩ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፤ ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት በውይይት መፍትሄ አግኝቷል ሲባል፤ አቶ ለማ ወደ ሚዲያ ወጥተው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ ብለው የጠበቁ በርካቶች ነበሩ።

አቶ ሳዳት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አቶ ለማ ለመገናኛ ብዙኃን እንዳይናገሩ ክልከላ ተደርጎባቸዋል የሚባለው ከጥርጣሬ የመነጨ ነው ይላሉ። "ልዩነቱ በውይይት ተፈትቷል። ይሄ እውነት ነው። ውይይቱ ከተካሄደ በኋላ በመግባባት እየተሰራ ይገኛል። አሁንም በኃላፊነት ላይ ነው ያሉት" ይላሉ አቶ ሳዳት።

"አቶ ለማ ካልተናገሩ በቀር የፓርቲው መግለጫ ስህተት ነው ብሎ ማሰቡ ትክክል አይደለም። በፓርቲው የተሰጠው መግለጫ፤ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እና የጓድ ለማ አቋም ሆኖ መታየት አለበት" ብለዋል አቶ ሳዳት።

የመካከለኛ እና ዝቅተኛ ደረጃ ባለልጣናት ሹም ሽር

በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ ከመካከለኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ባሉ ባለሥልጣናት ላይ ሹም ሽር እየተካሄደ ይገኛል።

ቀላል የማይባሉ የክልሉን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ግለሰቦች ከሥራ እንዲነሱ እየተደረጉ ያሉት፤ የአቶ ለማ ሃሳብ ደጋፊዎች ናቸው የሚሉ መላምቶችን የሚሰነዝሩም አልጠፉም።

አቶ ሳዳት ግን፤ "ፓርቲው በራሱ ምዛኔ ባለሥልጣናትን ከቦታ ቦታ ያሸጋሽጋል። ምደባም ይሰጣል። እንዲህ አይነት ሹም ሽሮች የሚካሄዱት በአመለካከት ልዩነት ላይ ተመስረቶ አይደለም"

"በአሁኑ ሰዓት 'የፓርቲ አስተሳሰብ' እንጂ 'የአቶ ለማ ሃሳብ' የሚባል ነገር የለም" በማለት የነበሩ ልዩነቶች መፈታታቸውን አቶ ሳዳት አስረግጠው ይናገራሉ።

አቶ ለማ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጎልተው የወጡባቸው አጋጣሚዎች

በወቅቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተለይ ደግሞ በክልላቸው ፖለቲካ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው የማይካደው አቶ ለማ፤ ከፍ ሲል "ለመውደቅና ለመበታተን ከጫፍ ደርሳ የነበረችውን ኢትዮጵያ በአንድነቷ እንድትቀጥል ያደረጉ ሰው ናቸው" ተብለው እስከ መወደስ ይደርሳሉ።

ለመሆኑ አቶ ለማ በኢትዮጵያ እና በክልሉ ፖለቲካ ውስጥ ጎልተው እንዲወጡ ያስቻሏቸው አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?

"ማስተር ፕላን"

2008 ዓ.ም የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተሰኘውን እቅድ በመቃወም በኦሮሚያ ሕዝባዊ ተቃውሞ የተቀጣጠለበት ዓመት ነበር።

ታዲያ የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ማስተር ፕላኑ መተግበሩ እንደማይቀር በሚናገሩበት ወቅት፤ አቶ ለማ የሕዝቡን ተቃውሞ ለማርገብ ከቡራዩ እና አካባቢው ነዋሪዎቸ ጋር ውይይት ሲያደርጉ "ማስተር ፕላኑ ሕዝብ ካልፈለገው ይቀራል፤ ከሰማይ የሚወርድ ነገር የለም" የሚል ይዘት ያለው ንግግር አድርገው ነበር።

ይህ ንግግራቸው ከፍተኛ ድጋፍ ያስገኘላቸው ሲሆን፤ ብዙም ሳይቆይ የክልሉ ፕሬዝደንት ሆነው ተሾሙ።

የለማ ቡድን "ቲም ለማ"

አቶ ለማ የኦህዴድ ሊቀ መንበር እና የክልሉ ፕሬዝደንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ እርሳቸው የመረጧቸውን አባላት በመመልመል 'ቲም ለማ' የተሰኘ ቡድን እንዳቋቋሙ ይነገራል።

ይህ ቡድን ሕዝቡ በወቅቱ ያነሳቸው ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ጥረት ያደርግ ነበረ። በዚያን ወቅትም የክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦህዴድ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ 'ኦሮምኛ የፌደራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን እታገላለሁ" ያለው።

ተከትሎም በሺህዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ከእስር መልቀቁ ፓርቲው በኦሮሚያ ያለው ድጋፍ እንዲጨምር አድርጎለት ነበር።

'ጌታችን ዝባችን'

ጥር 4/2008 የኦህዴድ 27ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓልን በማስመልከት በአዳማ ከተማ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ አቶ ለማ ለፓርቲያቸው አባላት ". . . ጌታችን ሕዝባችን ነው። የክልላችን ሕዝብ ነው። ለሌላ ጌታ መስገድ የለብንም" በማለት ተናግረው ነበር።

ይህ የአቶ ለማ ንግግር ህውሓት በኦህዴድ ላይ የነበረውን የበላይነት የሰበረ ነው በማለት አንዳንድ ድርጅቱንና የአገሪቱን ፖለቲካ በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ።

"ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው"

ከለውጡ ማግስት ጀምሮና በተከታይ በነበሩት ጊዜያት አቶ ለማ በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙበት ወቅት ነበር።

ከዚህ ቀጥሎ ያደረጉት ንግግር ከክልላቸው አልፎ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝብ ወንድማማችነትን ለማጠናከር ባለመው መድረክ ላይ "ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው" በማለት ያደረጉት ንግግር በበርካቶች ተወዳጅነትን አስገኝቶላቸዋል።