ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጋምቤላ፡ በክልሉ የአንበሳ 'ቡድን' ሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ተባለ
በጋምቤላ ክልል አቦቦ ወረዳ ባለፉት 12 ወራት ብቻ የአንበሳ ቡድኑ 5 ሰዎችን መብላቱን እና በአንድ ሰው ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት ማድረሱን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ኡሞ ቱቶ ለቢቢሲ ተናገሩ።
አቶ ኡሞ ቱቶ እንደሚሉት የአንበሳው ቡድን በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በመጥቀስ የፌደራል የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን እርምጃ አንዲወስድ ቢያሳውቁም አሁንም አንበሳ በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
“እንደ ክልል አንበሳ መግደል አንችልም። ሪፖርት ማድረግ ብቻ ነው የምንችለው” ብለዋል።
የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን የህብረተሰብ አጋርነት እና የዱር እንስሳት ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ካህሳይ ገ/ትንሳዬ በበኩላቸው “አጥፊው ቡድን ላይ እርምጃ የሚወስድ ቡድን ልከን አንድ አጥፊ ብቻ ነው የተቀነሰው” ብለዋል።
አቶ ካህሳይ “ይህ አጥፊ ቡድን” የአንበሳ መንጋ ሳይሆን የአንበሳ ቡድን ነው ይላሉ።
የሆነው ምንድነው?
አቶ ኡሞ በሚያስተዳድሩት ወረዳ ባለፈው አንድ ዓመት በአንበሳ ቡድኑ ጥቃት የደረሰው በተመሳሳይ በሐምሌ እና ነሐሴ ወራቶች መሆኑን ይናገራሉ።
“አምና ሁለት ሰዎች የተበሉት ሐምሌ እና ነሐሴ ወር ላይ ነበር። ዘንድሮም በሰዎቹ ላይ ጥቃት የደረሰው በሐምሌ እና ነሐሴ ወር ነው” ይላሉ። አቶ ኡሞ ይህ የሆነበትን ምክንያት ግን ለእነርሱም እንቆቅልሽ መሆኑን ያስረዳሉ።
አቶ ኡሞ በቅርቡ በአንበሳ የተበላው በሰሊጥ እርሻ ላይ በቀን ሰራተኛነት የሚተዳደር እና እድሜው ወደ 30 ዓመት የሚጠጋ ወጣት ሲሆን ቅዳሜ ነሐሴ 23/2012 ከሥራ ወጥቶ በመንገድ ላይ እየተጓ ሳለ በአንበሳ መበላቱን ይናገራሉ።
በሐምሌ ወር ላይም በአንበሳ የተበላው ግለሰብ በእርሻ ልማት ላይ የቀን ሰራተኛ ሆኖ የሚሰራ ሰው እንደነበር አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
በቅርቡ በአንበሳ ከተበሉት መካከል ሌላኛው ሴት መሆናቸው እና እርሳቸው ከምሽቱ 12 ሰዓት አከባቢ በመንገድ በእግር እየሄዱ ሳለ በአንበሳ መበላታቸውን ይናገራሉ።
“ሴትየዋ ወደ ሌላ ቀበሌ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆና እየሄደች ነበር። ብቻዋን ወደ ኋላ ስትቀር ነው የተበላችው” ብለዋል አቶ ኡሞ።
ከባድ ጉዳት ያጋጠመው ግለሰብ ደግሞ መቀመጫው ላይ በአንበሳው ክፉኛ መነከሱን እና የህክምና ክትትል እየተደረገለት መሆኑን አስረድተዋል።
እስካሁን በወረዳው በአንበሳ ጥቃት የተሰነዘረባቸው ሰዎች በዱር ውስጥ ሳይሆን መንገዶች ላይ በእግራቸው ሲራመዱ መሆኑን ያስታውሳሉ።
መፍትሄው ምንድነው?
“እኛ እንደ ክልል የዱር እንስሳ መግደል አንችልም። ለዱር ጥበቃ እና ልማት ሪፖርት ማድረግ ብቻ ነው የምናደርገው” የሚሉት አቶ ኡሞ ሰዎች ከመሸ በእግር ከመጓዝ እና ከቤት ከመውጣት እንዲቆጠቡ ብቻ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።
“ከመሸ ሰው መንቀሳቀስ እንደሌለበት እያሳወቅን ነው። እያደረግን ያለነው ይህን ብቻ ነው” ብለዋል።
“ችግር ፈጣሪ አንበሶችን የሚቀንስ ቡድን ልከናል”
በዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን የህብረተሰብ አጋርነት እና የዱር እንስሳት ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ካህሳይ ገ/ትንሳዬ በጋምቤላ ክልል በአንበሳ ቡድን እየደረሰ ያለው ጉዳት እየተባባሰ ስለመምጣቱ መረጃው አለን ይላሉ።
“ወደ ጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ቡድን ልከን ነበር። ይህ ቡድን ጥናት አካሂዶ ችግር ፈጣሪ የሆኑ አናብስት መኖራቸውን እና መቀነስ አለባቸው የሚል ምክረ ሃሰብ አቅርቧል” ይላሉ።
አቶ ካህሳይ “ችግር ፈጣሪ” የተባሉ አንበሶችን “የሚቀንስ” ቡድን ወደ ስፍራው ተልኮ ለሦስት ሳምንታት የአደን ሥራ ላይ ቢቆይም “የተቀነሰው አንድ ችግር ፈጣሪ አንበሳ ብቻ ነው” ይላሉ።
አቶ ካህሳይ፤ ወደ ጋምቤላ ከተላከው አንበሳ አዳኝ ውስጥ የውጪ ዜጎች እንዲካተቱ መድረጉን ጨምረው ተናግረዋል።
“በሕጋዊ አደን የውጪ ሰዎች መጥተው እንዲያድኑ አድርገናል። የተሻለ መሳሪያ፣ ልምድ እና ክህሎት አላቸው። ከደቡብ አፍሪካ የመጡ አዳኞች ሦስት ሳምንት ቢቆዩም እርምጃ መውሰድ የተቻለው ግን በአንድ ችግር ፈጣሪ አንበሳ ላይ ብቻ ነው” ብለዋል።
ወደፊትም ቢሆን ጥናት ላይ የተመረኮዘ እርምጃ እንደሚወሰድ አቶ ካህሳይ ተናግረዋል።
አቶ ካህሳይ አንበሶችን “የመቀነስ” አማራጭ የሚወሰደው እንደ መጨረሻ አማራጭ እንደሆነም ያስረዳሉ።
“ችግር ፈጣሪ የሚባለው ባህሪውን ሲቀይር ነው”
አቶ ካህሳይ አንበሶቹ ችግር ፈጣሪ ሆነዋል የሚባለው ባህሪያቸው ሲቀየር መሆኑን ያስረዳሉ።
“የሚበሉ የዱር እንስሳት እያሉ ባህሪውን በመቀየር በተደጋጋሚ የቤት እንስሳት የሚበላ እና ሰው ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርስ ከሆነ አጥፊ ይባላል” ይላሉ።
የዱር እንስሳት “አጥፊ” ወደሚባል ደረጃ ከሚዳርጓቸው ምክንያቶች መካከል የመጀመሪያው በእንስሳቱ ላይ ከማህብረሰቡ ትንኮሳ ሲያጋጥማቸው ነው።
“በአንበሶች መኖሪያ አከባቢ መስፈር፣ ከአንበሳ ባህሪ ጋር አብረው የማይሄዱ ድርጊቶችን መፈጸም የአንበሳ ባህሪ እንዲቀየር ያደርጋል” ይላሉ አቶ ካይሳይ።