ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ ግለሰቡን በልቶ የተሰወረው አንበሳ እየታደነ ነው
የኬንያ የዱር እንስሳት አገልግሎት በዋና መዲናዋ ናይሮቢ ዳርቻ በሚገኝ የመኖሪያ መንደር አካባቢ አንድን ግለሰብ የበላውን አንበሳ እያደነ መሆኑን አስታወቀ።
አሁንም አንበሳውን የመፈለግ ሥራው በመቀጠሉ ነዋሪዎች ቤት ውስጥ እንዲያሳልፉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
በሮንጋይ አካባቢ በአንበሳ የተባለው ግለሰብ አስክሬን ቀሪ ክፍል ትናንት ሰኞ መገኘቱን ተከትሎ አሁንም ጭንቀት እንደነገሰ ነው።
ግለሰቡ ከናይሮቢ ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ አምልጦ እንደወጣ በተነገረው አንበሳ ግማሹ የአካል ክፍሉ ተበልቷል።
የኬንያ የዱር እንስሳት አገልግሎት በመግለጫው፤ በግለሰቡ ሞት የተሰማውን ሀዘን ገልፆ፤ ግለሰቡን የበላውን አንበሳ አድኖ ለመያዝ የፓርክ ጠባቂዎች እና የእንስሳት ሐኪም ቡድን መላኩን አስታውቋል።
አንበሳው በቁጥጥር ሥር እስከሚውልም ድረስ የአካባቢው ማሕበረሰብ በምሽት ቤታቸው ውስጥ እንዲያሳልፉ አሳስበዋል።
ከናይሮቢ ብሔራዊ ፓርክም ሆነ ከሌሎች የዱር አንስሳት ፓርኮች በተለይ አንበሳ አምልጦ መውጣት ያልተለመደ ቢሆንም፤ ፓርኮቹ ለከተማዋ ቅርብ በመሆናቸው ለእንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ክስተቶች ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል።
ከዚህ ቀደም እንስሳት ፈጣን መንገድን ዘግተው እንደነበር በድርጊቱ የተደነቁ ተጓዦች ምስላቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ገፆች ላይ ማጋራታቸው ይታወሳል።