ትራምፕ አሜሪካ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚ መሆኗ 'ክብር' ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳነት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በተረጋገጡ ሰዎች ብዛት ከዓለም ቀዳሚ መሆኗ "ክብር" ሊያሰጣት እንደሚገባ ተናገሩ።
ዋይት ሐውስ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ላይ "ይህንን ነገር በተለየ መልኩ ነው የምመለከተው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ "የተገኘው ውጤት እንደ ጥሩ ነገር ነው የማየው። ምክንያቱም ይህ የምናደርገው ምርመራ ከሁሉም የተሻለ መሆኑን ያሳይል" ብለዋል።
የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ በሚያወጣው መረጃ መሰረት በአሜሪካ በአሁኑ ጊዜ 1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን 92 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ህይወታቸውን አጥተዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአሜሪካ ከተከሰተ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኞ ዕለት ባካሄዱት የካቢኔ ስብሰባቸውን ያካሄዱት ፕሬዝዳንቱ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት አገራቸው በበሽታው በተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚ የሆነችው ከየትኛውም አገር በበለጠ ምርመራ በማድረጓ መሆኑን አመልክተዋል።
ጨምረውም "በርካታ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሲኖረን በአንድ መልኩ እንደ መጥፎ ነገር አላየውም ምክንያቱም ምርመራችን የተሻለ መሆኑን ስለሚያመለክት" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጨምረውም የተገኘው ውጤትን "እኔ እንደ ክብር ምልክት ነው የማየው። በአውነትም የከብር ምልክት ነው። የተገኘው ውጤት በመመርመር እና በተለያዩ የህክምና መስኮች ላይ የተሰማሩት ባለሙያዎች ላከናወኑት ሥራ የተገኘ ውጤት ነው" ብለዋል።
የተቀናቃኛቸው ዲሞክራቲክ ፓርቲ ብሔራዊ ኮሚቴ ግን ከሪፐብሊካን ፓርቲ የመጡትን ፕሬዝዳንት በዚህ ንግግራቸው ተችቷቸዋል።
ፓርቲው በፕዊትር ገጹ ላይ እንዳሰፈረው በአሜሪካ 1.5 ሚሊዮን የኮቪድ-19 ህሙማን መገኘታቸው የሚያስከብር ሳይሆን "የአመራሩን ፍጹም ውድቀት" የሚያመለክት ነው ብሏል።
የአሜሪካ መንግሥት የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ባወጣው መረጃ መሰረት በመላው አገሪቱ በ12.6 ሚሊዮን ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጓል።














