ለ20 ዓመታት ሲፈለግ የነበረው ዕፅ አዘዋዋሪ አፍሪካ ውስጥ ተያዘ

የሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ

ላለፉት 20 ዓመታት በፖሊስ ሲታደን የነበረውና በብራዚል እጅግ ተፈላጊ የአደገኛ ቦዘኔዎች አለቃ በአፍሪካዊቷ ሞዛምቢክ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነገረ።

ይህ ግለሰብ ጊልቤርቶ አፓርሲዶ ዶስ ሳንቶስ ሙሉ ስሙ ሲሆን በይበልጥ የሚታወቀው ግን ፉሚንሆ በሚለው ቅጽል ስሙ ነው።

ፉሚንሆ በአደገኛ ዕፅ ዝውውር የብራዚል ዋናውን የአደገኛ ቦዘኔዎች ቡድን የሚመራ አለቃ ነበር። አሁን 49 ዓመቱ ሲሆን ላለፉት 20 ዓመታት ደብዛው ጠፍቶ ፖሊስ ያለበትን ሲያስስ ደክሟል።

ነገር ግን በድንገት እዚህ አፍሪካ ውስጥ በሞዛምቢኳ ዋና ከተማ ማፑቶ ውስጥ ተገኝቷል።

ግለሰቡን አፈላልጎ ለመያዝ ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል፣ ብራዚልና የአሜሪካ የጸረ አደገኛ ዕፅ ግብረ ኃይል የተቀናጀ ሥራ ማከናወናቸው ተነግሯል።

ፉሚንሆ በብራዚል ቁጥር አንድ አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪ የቦዘኔዎች ቡድን የሆነው 'ፈርስት ካፒታል ኮማንድ' የተባለው ቡድን አለቃ ነበር። ይህ የአደገኛ ቦዘኔዎች ሰንሰለት በመላው ዓለም ኮኬይን የተባለውን ዕፅ በማከፋፈል እውቅ ስም ነበረው።

ፉሚንሆ የተያዘው ማፑቶ በሚገኝ ሞቴንቤሎ ኢንዲ በሚባል ቅንጡ ሆቴል ውስጥ ከሁለት ናይጄሪያዊያን ጋር ነው ተብሏል።

በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት በርካታ ገንዘቦች፣ ሐሰተኛ ፓስፖርቶች በርካታ ስልኮች በኤክዚቢትነት በፖሊስ ተይዘውበታል።

ፉሚንሆ የሌላ አደገኛ እጽ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ የነበረውን ካማቾ የተባለውን ሰው ከእስር ቤት በማስመለጥ ይጠረጠራል። ካማቾ በወንጀል ስሙ ማርኮሎ አሁን 200 ዓመት ተፈርዶበት በብራዚል እስር ቤት ይገኛል።

እስካሁን ሞዛምቢክ ተጠርጣሪው ፉሚንሆን በአገሩ ለፍርድ እንዲቀርብ ለብራዚል አሳልፋ ትሰጠው እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።