ሞዛምቢክ '1.5 ቶን ሄሮይን ሲያጓጉዙ' የነበሩ 12 ኢራናውያንን በቁጥጥር ሥር አዋለች

በእሳት የምትነድ ጀልባ

የፎቶው ባለመብት, Mozambique Defence Force

ሞዛምቢክ ሕንድ ውቅያኖስ ላይ ግምቱ ከ1.5 ቶን በላይ ሄሮይን ሲያጓጉዙ የነበሩ 12 የኢራን ዜጎችን በቁጥጥር ሥር አዋለች።

ሄሮይን የተሰኘውን አደገኛ አደንዛዥ ዕጽ ሲያጓጉዙ ነበሩ የተባሉት 12ቱ ኢራናውያን የተያዙት ከሞዛምቢክ ሰሜናዊ አቅጣጫ ሕንድ ውቅያኖስ ላይ ነበር።

አደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎቹ ሲጓዙባት የነበረችው መካከለኛ ጀልባ በሞዛምቢክ ባህር ኃይል እና የሃገሪቱ ወንጀል ምርመራ ቡድን ስትከበብ ተጠርጣሪዎቹ ጀልባዋን በእሳት አጋይተው ወደ ውቅያኖሱ ዘለዋል።

ወደ ሕንድ ውቅያኖስ ከዘዘሉት መካከል 3ቱ ህይወታቸው ሲያልፍ 12ቱ ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የሞዛምቢክ ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ ተጠርጣሪ እጽ አዘዋዋሪዎቹ በጀልባዋ ላይ ተጭኖ የነበረ ወደ 1.5 ቶን የሚገመት ሄሮይን በእሳት አጋይተዋል።

12ቱ ኢራናውያን ፔምባ ወደምትሰኝ ከተማ ተወስደው በፖሊስ ምረመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል።

የሞዛምቢክ መንግሥት ይህ ኦፕሬሽን ያካሄደው ከተለያዩ ምንጮች የደረሱት መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ እንደሆነ አሳውቋል።