ኮሮናቫይረስ፡ ሰዎች ለምን ስለኮሮናቫይረስ የሚነገሩ ሐሰተኛ ወሬዎችን ያምናሉ?

ከተማሪዎች እስከ ፖለቲከኞች ያሉ ብዙ ብልህ ሰዎች ስለኮሮናቫይረስ በተሰራጩ አደገኛ ውሸቶች ተታለዋል። ለምን? እንዴት እራስዎን ከተሳሳተ መረጃ መጠበቅ ይችላሉ?

ማንኛውም የጤና ቀውስ የራሱ የሆነ የተሳሳተ የመረጃን መቅሰሱ የሚያሳዝን እውነት ነው።

በተለያዩ ወቅቶች ስለኤድስ የሐሰት ወሬዎች ተሰራጭተው አይተናል። የኤችአይቪ ቫይረስ በመንግሥት በቤተ ሙከራ ውስጥ እንደተፈጠረ፤ የኤችአይቪ ምርመራዎች እምነት የማይጣልባቸው ናቸው የሚሉ ወረሬዎችን ሰምተናል።

አልፎ ተርፎም ሊታመን በማይችል መልኩ በሽታው በፍየል ወተት ሊታከም እንደሚችል በስፋት ሲነገር ነበር። ነገር ግን እነዚህ ሐሰተኛ መረጃዎች የሰዎችን ተጋላጭነት ከማስፋት ባሻገር ቀውሱን ያባብሳሉ።

አሁን ደግሞ ተራው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነው። ከፌስቡክ እስከ ዋትስአፕ ድረስ ከወረርሽኙ አመጣጥ ጀምሮ እስከ መከላከያው ድረስ ብዙ የተጋሩ የተሳሳቱ መረጃዎችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

ከፀሐይ ብርሃን አስከ ሞቃት የአየር ሁኔታ እንዲሁም ትኩስ ውሃ መጠጣት የኮሮናቫይረስ መስፋፋት ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩበት የተነገሩ በርካታ ሐሰተኛ መረጃዎችን ቢቢሲ አጋልጧል።

ከዚህ አንጻር በጣም መጥፎው ነገር የሚሰራጩት የሐሰት ወሬዎች ራሳቸው ጎጂ መሆናቸው ነው። ከወደ ኢራን የተገኘ አንድ ሪፖርት እንዳመለከተው ከኮቪድ-19 ያድናል በሚል ብዙዎች ጠንካራ አልኮል በመጠጣታቸው ምክንያት ሞተዋል።

የፈጠራ የሚመስሉ ሃሳቦች እንኳን ወደ ተሳሳተ የደኅንነት ስሜት ውስጥ ከማስገባት ባለፈ ሰዎች የመንግሥት መመሪያዎችን እንዳይከተሉ እና በጤና ባለስልጣኖችና በድርጅቶች ላይ ያለን አመኔታ ያሳጣሉ።

ለዚህ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል። ዩጎቭ እና ዘ ኢኮኖሚስት ባለፈው ወር ባደረጉት አንድ ጥናት እንዳመለከቱት 13 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካዊያን የኮቪድ-19 ቀውስ ውሸት ነው ብለው ያምናሉ። 49 በመቶዎቹ ደግሞ ሰው ሰራሽ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

እናም የማገናዘብ ብቃት ወይም ትምህርት እውነቱን ለመለየት ሊረዳን ይችላል የሚል ተስፋ ቢኖርም በእነዚህ የሐሰት መረጃዎች የተታለሉ ብዙ የተማሩ ሰዎችን ማግኘት ቀላል ነው።

ታዋቂዋ የኮቪድ-19 ሴራ ተንታኟ ጸሐፊ ኬሊ ብሮጋንን ብቻ አስቡ። ከማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም ዲግሪ ያላት ሲሆን በኮርኔል ዩኒቨርስቲ ደግሞ ሥነልቦናን አጥንታለች። ሆኖም እንደ ቻይና እና ጣሊያን ባሉ ሀገሮች ውስጥ ቫይረሱ ያደረሰውን አደጋ አትቀበለውም።

ይህንን ክስተት በዝርዝር ለመረዳት የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ጥናት እያደረጉ ነው። በመጨረሻም የሚደርሱበት ግኝት ምናልባት ራሳችንን ከውሸት የምንጠብቅበት አዲስ መንገድ ሊጠቁሙና የተሳሳተ መረጃን መስፋፋት ለማስቆም ሊረዳ ይችላል።

መጠነ ብዙ የመረጃ

የተወሰነው የችግሩ ክፍል መነሾ በመልዕክቶቹ ተፈጥሮ ላይ ነው።

በየቀኑ ብዙ መረጃ ይደርሰናል። ስለሆነም ብዙውን ጊዜ አንድ ነገር ትክክል መሆኑን ለመወሰን በፍላጎታችን እንመራለን። ከዚህ በፊት ቢቢሲ እንደገለፀው የሐሰት ዜና አዘጋጆች በቀላሉ ሠርተን እውነታውን እንዳናውቅ መልእክቶቻቸው "እውነት" እንዲመስሉ ያደርጋሉ።

ለምሳሌ ምስልን ከመግለጫ ጋር ማቅረብ በእውነታው ላይ ያለንን እምነት ይጨምረዋል። የአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ ኢሪ ኒውማን ያስረዳሉ። ከቫይረሱ ምስል ጋር የቀረበ ጽሑፍ ማረጋገጫ ባይኖረውም ጥቅል ጉዳይን እንድናስብ ያደርገናል፤ እንደእውነታም እንወስደዋለን።

በዚህ ምክንያት የተሳሳተ መረጃ ገላጭ ቋንቋን ወይም ግልጽ የግል ታሪኮችን ያጠቃልላል። እንዲሁም እንደ ታዋቂ ህክምና ተቋም ያሉ የምናውቃቸውን እውነታዎችና ቁጥሮችን በመጨመር ከእውቀታችን ጋር በማዛመድ አሳማኝ ይመስላሉ።

ድግግሞሽ እንኳን መላመድን ፈጥሮ "እውነታነትን" ሊፈጥር ይችላል። መጀመሪያ ብንጠራጠርም ተደጋግሞ የመጣን ነገርን እውነት ነው ብለን እናስባለን።

ከማሰብ በፊት መጋራት

የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ብዙ ሰዎች አንድን ይዘት ስለትክክለኛነቱ እንኳን ሳይያስቡ እንደሚጋሩ ነው።

ካናዳ በሚገኘው ሬጂና ዩኒቨርሲቲ ሐሰተኛ መረጃን የሚያጠኑት የሥነ ልቦና ተመራማሪው ጎርደን ፔኒኩክ ለጥናታቸው ተሳታፊዎች ስለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የእውነተኛ እና የሐሰተኛ አርዕስቶች ድብልቅ እንዲመለከቱ ጠየቁ።

ስለእያንዳንዱ አርዕስት እውነተኛነት ሲጠየቁ 25 በመቶ ያህል ጊዜ ሐሰተኛ ዜናዎቹ እውነተኛ ናቸው ብለዋል። ስለማጋራት ሲጠየቁ 35 በመቶዎቹ ሐሰተኛ ዜናውን እንደሚያጋሩ ተናግረዋል።

ምናልባትም አንጎላቸው ትክክለኛነቱን ከማጤን ይልቅ ምን ያህል 'ላይክ' እና 'ሪትዊት' እንደሚያገኝ በማሰብ ላይ አተኩሯል። "ማኅበራዊ ሚዲያ እውነትን አያበረታታም። እውነታው ያለው ሼር እና ላይክ ላይ ነው" ይላሉ ፔኒኩክ።

ምናልባትም ኃላፊነትን ወደ ሌሎች እነዳሳለፉ ተሰምቷቸው ይሆናል። ብዙ ሰዎች ከላይ "ይህ እውነት ስለመሆኑ አላውቅም፤ ግን…" የሚል ነገር በመጻፍ መረጃ እያጋሩ ነው።

መረጃው እውነትነት ካለው ለጓደኞችና ተከታዮች ሊጠቅም ይችላል፤ እውነት ካልሆነ ግን አይጎዳም በሚል ነው። ስለዚህ ማበረታቻው ማጋራት ነው። ግን ማጋራትም ጉዳት ያስከትላል ብሎ አለማገናዘብ ነው።

የደመ ነፍስ ምላሽን መቆጠጠር

ሥነ-ልቦናዊ ምርምር እንደሚያሳየው አንዳንድ ሰዎች ተፈጥሮአዊ የሆኑ የደመ ነፍስ ምላሾቻቸውን በመቆጣጠር በኩል ከሌሎች ይልቅ የተሻሉ ናቸው። ይህ ግኝት አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ለሐሰት ዜናዎች የበለጠ የሚጋለጡበትን ምክንያት እንድንገነዘብ ይረዳናል።

ብልህ እና የተማሩትም ጨምሮ ብዙዎች በሐሰተኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ የተሳሳተ አመለካከት እንዳላቸው ማወቃችን የተሳሳተ መረጃ መስፋፋትን ለማስቆም ይረዳናል።

ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከልም ድርጅቶች የተወሳሰበ አገላለጽን ከመጠቀም መቆጠብ ያስልጋቸዋል። ይልቁን እውነታውን በቀላል ዘዴ ማቅረብ አለባቸው። ሀሳቦችን በቀላሉ ለመሳል ምስሎችን እና ግራፎችን በመሳሰሉ ዘዴዎች በመጠቀም ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

ከቻሉ ሃሰተኛ መረጃዎችን ከመድገም መቆጠብ አለባቸው። መደጋገም ሀሳቡን የበለጠ የታወቀ አድርጎ እንደእውነት የመቀበል ዕድሉን ይጨምረዋል። ነገር ግን ይህ ሁልጊዜ ሊሆን አይችልም።

ዘመቻዎች ግን ከሐሰተኛ መረጃዎቹ ይልቅ እውነታዎች የበለጠ ጎልተው እንዲታዩ እና የማይረሱ በማድረግ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ተቀርጸው የመቆየት ዕድላቸውን ማሳደግ ይችላሉ።

እኛም በይዘቱ ካለው ስሜት ለመራቅ ልንሞክር እና ከማጋራታችን በፊት ስለ እውነታው ትንሽ ለማሰብ እንሞክራለን።ስለዚህም ስለምናጋራቸው መረጃዎች የሚከተሉትን ጥያቄ መመለስ ያስፈልገናል።

በሰማ በለው ነው ወይስ በጠንካራ ሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ነው? ወደ መጀመሪያው ምንጭ ብንመለስ መረጃውን ማግኘት እንችላለን? አሁን ካለው መረጃ ጋር እንዴትስ ይነፃፀራል?

ለሌሎች ይጠቅማል ወይም 'ላይክ' ያመጣል ከማለት በፊት ልንጠይቃቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ናቸው። እናም ሁላችንም ይህንን ዓይነት አስተሳሰብ በተግባር በመለማመድ የተሻልን መሆን እንደምንችል ማስረጃዎች ያሳያሉ።