ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ከኮቪድ-19 ያገገሙት የአዳማ ነዋሪ ምን ይላሉ?
"ወንድ ልጄን ኮሪደር ላይ ሳየው በጣም ደነገጥኩኝ፤ ጮኬ ወደቅኩ። ቤተሰቦቼ በአጠቃላይ እዚያ ያሉ ነው የመሰለኝ" ይህን ያሉት በአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና በኮቪድ-19 ተይዘው የነበሩት የፋርማሲ ባለሙያ ናቸው።
በኮሮናቫይረስ መያዛቸው እንደታወቀ የተወሰዱት አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሲሆን፤ እዚያ ተኝተው በሚታከሙበት ወቅት ልጃቸውን ማየታቸውን የፈጠረባቸውን ስሜት ነበር ለቢቢሲ ያጋሩት።
አቶ ዳግማይ በቀለ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ናቸው፤ ከሁለት ሳምንት በፊት መጋቢት 18/2012 ዓ.ም ነበር በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ጤና ጥበቃ ያስታወቀው።
እኚህ የ61 ዓመት አዛውንት አዲስ አበባ በሚገኘው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው በአሁን ጊዜ ከቫይረሱ በማገገማቸው አዳማ ወደ ሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰዋል።
የፋርማሲ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳግማይ፣ ቫይረሱ እንዴት ሊይዛቸው እንደቻለ እንደማያውቁ ይናገራሉ፤ ነገር ግን አንዳንድ ምልክቶችን በማየታቸው ራሳቸውን ለመለየት ስለፈለጉ ከቤተሰባቸው ርቀው ሆቴል ተከራይተው መቀመጣቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"ራሴን ስለጠረጠርኩኝ ከዚህ እስከምወጣ ማንም ሰው እኔ ጋር እንዳይመጣ፤ ከመጣም የእጅ ጓንትና ጭምብል አድርጎ ይምጣ በማለት ለሆቴሉ ሠራተኞች ጭምር ተናግሬ ነበር" ብለውናል።
የኮቪድ-19 ምልክቶች የተባሉትን ራሳቸው ላይ ማየት እንደጀመሩ አዳማ ከተማ ወዳሉ የጤና ተቋማት መሄዳቸውን ይናገራሉ።
እንደ አቶ ዳግማይ ከሆነ ማንም ቫይረሱ አለብህ ሊላቸው አልቻለም።
ከዚያም ይላሉ አቶ ዳግማይ "ወደ ጤና ጥበቃ ደውዬ ያመኛል ነገር ግን የሚመረምረኝ ሰው አላገኘሁም ብዬ ነገርኳቸው። ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወደ ኦሮሚያ ጤና ቢሮ ከዚያም ወደ አዳማ ከተማ ተደውለ" በማለት በወቅቱ እንዴት መመርመር እንደቻሉና ቫይረሱነም እንደተገኘባቸው ያስረዳሉ።
አቶ ዳግማይ በቀለ የኮቪድ-19 በማስመልከት አዳማ ላይ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል ነበሩ። መጀመሪያ ደረቅ ሳል ያስለኝ ነበር የሚሉት አቶ ዳግማይ በመቀጠልም ጉሮሮዋቸው ውስጥ የመብላት የማሳከክ ስሜት እንደጀመራቸው ይናገራሉ።
"ኮሮና ይሆን ብዬ በቀልድ ሳወራ ሰዎች አይ አይደለም ሳይነስ ነው የተነሳብህ እንጂ ኮሮና አይደለም ይሉኝ ነበር።"
በመቀጠልም ከባድ ራስ ምታት እንደጀመራቸውና ሰውነታቸውም መደካከም እንደጀመረ ያስታውሳሉ።
"ትንሽ ያሳሳተኝ የሰውነቴ ሙቀት ረዘም ላለ ጊዜ ከ36 በልጦ አያውቅም፤ ሁልጊዜም ከሦስት እስከ አራት በሚሆን ሰዓት ልዩነት ውስጥ የሰውነቴን ሙቀት እለካ ነበር። ከዚያ በኋላ አንድ ቀን ማለዳ ስለካ ሙቀቴ 38 ሆኗል፤ በዚህ ጊዜ እርሱ ነው[ኮሮና] ብዬ መያዜን ተጠራጠርኩኝ።"
ከዚህ በኋላ የድጋፍ አሰባሳቢው ኮሚቴ ስብሰባ መካፈል ማቆማቸውን ይገልፃሉ።
የኤካ ኮተቤ ቆይታና ድንጋጤ
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች የሚቆዩበትና ህክምና የሚከታተሉበት ሆስፒታል ነው።
በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ከ20 ቀናት በላይ እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ ዳግማይ በሆስፒታሉ ውስጥ ከ10 ቀን በላይ ከባድ ህመም ላይ እንደነበሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የህክምና ባለሙያዎችም የሜካኒካል ቬንትሌተር ገጥመውልኝ እና የተለያዩ መድኃኒቶች ሲሰጡኝ ነበር" በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ለሰባት ወይንም ለስምንት ቀናት ምግብና ውሃ እንዳልወሰዱ ከወሰዱም ደግሞ ያስመልሳቸው እንደነበር ያስረዳሉ።
አቶ ዳግማይ በከባድ ህመም ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ባለቤታቸውና የ14 ዓመት ወንድ ልጃቸው በበሽታው ተይዘው ወደ ሆስፒታሉ መጡ።
"ለሦስትና ለአራት ቀን ደብቀውኝ አልተገናኘንም ነበር" የሚሉት አቶ ዳግማይ "እኔም በወቅቱ ከባድ ህመም ላይ ነበርኩ" ብለዋል።
እርሳቸው ወደ ሆስፒታል ከገቡ ከሦተኛው ቀን በኋላ ወደ ባለቤታቸው በመደወል መያዛቸውን መስማታቸውን ይገልፃሉ።
በዚህ ወቅት ስለልጆቻቸው ጤንነት የጠየቁት አቶ ዳግማይ ሁሉም ደህና መሆናቸው እንደተነገራቸው ገልፀዋል። ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ ባለቤታቸው የተኙበት ክፍል ድረስ በመምጣት ሲያናግሯቸውና እርሳቸውም መያዛቸውን ሲግሯቸው አዘኑ።
ወንድ ልጃቸው በበሸታው እንደተያዘ ያልተነገራቸው አቶ ዳግማይ ልጃቸውን ሆስፒታል ውስጥ በማየታቸው ከባድ ስሜት እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።
"ከአምስት ቀን በኋላ ወደ ንጽህና መስጫ እየሄድኩኝ ልጄን ኮሪደር ላይ አየሁት በጣም ደንግጬ ጮህኩና ወደኩኝ፤ ከዚያ በኋላ ደብቀንህ ነው እንጂ እዚህ ከገባን አንድ ሳምንት ሆኖናል አሉኝ" ይላሉ።
አቶ ዳግማዊ፣ ባለቤታቸውና ልጃቸው በአሁኑ ሰዓት አገግመው አዳማ ወደሚገኘው ቤታቸው ተመልሰዋል።
በእርግጥ አቶ ዳግማይ አሁንም በመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ እንደሚተነፍሱ ነግረውናል። "እንደኔ ራሱን የሚጠብቅ ሰው የለም" የሚሉት አቶ ዳግማይ ሕዝቡ ስለኮሮናቫይረስ በደንብ ማወቅ አለበት ሲሉ ይመክራሉ።
የዓለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የሚሰጡትን ምክር መስማት ያስፈልጋል ሲሉም ያብራራሉ።
እጅን ቶሎ ቶሎ መታጠብ፣ ሳኒታይዘር መጠቀም፣ ከተቻለ የአፍ መሸፈኛ ማድረግ አለብን በማለትም መጨባበጥን ማስወገድና ርቀትን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ።
"ግዴታ የሌለባቸው ቤት መቆየት አለባቸው፤ ከቤት መውጣት አያስፈልግም፤ ቤት ሲሆኑም ደግሞ አልጋ ላይተኝቶ ቴሌቪዥን ማየት ብቻ ሳይሆን መጽሀፍ ማንበብ፤ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል። እኔ ራሴ አሁን ጠዋት ከ30 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ያህል ስፖርት ከልጄ ጋር እሰራ ነበር" ሲሉ ልምዳቸውን ያጋራሉ።
በመጨረሻም "ለራስ የምናስብ ከሆነ፣ ለሕዝብም እናስባለን፤ ይህንንም መጥፎ ወቅት አብረን እንሻገራለን፤ አገራችንንም እንጠብቃለን" ብለዋል።