ኮሮናቫይረስ፡ ደቡብ ኮሪያውያን ጭምብልና ክሊኒኮች በተዘጋጁበት ሁኔታ ምርጫ እያካሄዱ ነው

ደቡብ ኮሪያ በኮሮና ወቅትም ቢሆን ምርጫው ይካሄዳል ብላ በመወሰኗ መራጮች ወደየጣቢያው እየመጡ ነው።

ነገር ግን ዝም ብሎ በዘፈቀደ መምጣት የለም። ሁሉም የፊት ጭምብል ማድረግ እንዲሁም በአንድ ሜትር ተራርቀው መሰለፍ አለባቸው።

ከዚያም የሙቀት መጠናቸው ይለካል፣ እጃቸውንም በሳኒታይዘር እንዲያፀዱ ይደረግና የእጅ ጓንት ያጠልቃሉ።

እነዚህን ሁሉ ሂደቶች ካለፉ በኋላ ነው ድምፃቸውን ለመስጠት ወደተከለለው ሚስጥራዊ ቦታ የሚወሰዱት።

በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ እየተዛመተ ባለበት ወቅት የብሔራዊ ጉባኤው ምርጫ በተያዘለት እቅድ መሰረት እንዲካሄድ እነዚህ ቅድመ ጥንቃቄዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

ብሔራዊ ጉባኤው (ፖርላማው) ሶስት መቶ መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ ሰላሳ አምስት ፓርቲዎችም ተፎካካሪዎቻቸውን አቅርበዋል።

ነገር ግን በአብዛኛው ውድድሩ የሚሆነው በገዥው ፓርቲ ሚንጆ ዲሞክራቲክ ፓርቲና በተቀናቃኙ ወግ አጥባቂው ዩናይትድ ፊውቸር ፓርቲ መካከል ነው።

በምርጫው ላይ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመቆጣጠር እያደረገው ያለው ጥረት የምርጫ ውይይቶችን የበላይነት ስፍራ ይዞ ነበር።

ኮሮና ሊያስከትለው የሚችለውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ መሽመድመድ እንዲሁም ከፕሬዚዳንቱ የእርዳታ እቅዶች ጋር ተያይዞ ያሉ የሙስና ቅሌቶችም በብዙዎች ዘንድ ፍራቻን አንግሰዋል።

የብሔራዊ ጉባኤው ምርጫ ተመራጮች እንዲሁም የፓርቲዎች እውቅና የሚመዘንበት ሲሆን፤ ዋናው ምርጫ ግን የሚደረገው ከሁለት ዓመታት በኋላ ነው።

'የመምረጥ መብት'

የኮሮና ቫይረስ ፍራቻ በነገሰበት ሰአት ምርጫው ይካሄዳል መባሉ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችሉ ትችቶች እየተሰሙ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን ያስተዋልኩት በተረጋጋ ሁኔታ የተደረገ ምርጫ ነው።

መራጮች በተሰጣቸው ቦታ ላይ በፀጥታ ቆመው ተራቸውንም እየጠበቁ ነበር።

"ምናልባት ብዙ መራጭ ስለማይመጣ ምርጫው ቢራዘም የሚል ሃሳብ ነበረኝ። ነገር ግን እኔም መጥቻለሁ ብዙ ሰውም ለመምረጥ መጥቷል። የሚያስጨንቅ ነገር የለም" በማለት አንዲት ወጣት መራጭ ለቢቢሲ ተናግራለች።

የቫይረሱ የመዛመት ሁኔታ መራጮችንም ያሰጋ አይመስልም።

ከአስራ አንድ ሚሊዮን በላይ የሚበልጥ መራጭ፣ 26 በመቶ የሚሆነው አገሬው መርጧል። አንዳንዶች በፖስታ ምርጫቸውን ሲልኩ አብዛኞቹ ደግሞ ማልደው መጥተው መርጠዋል።

የተያዘው ህዝብ ቁጥርም ከፍተኛው ነው ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪ የ18 ዓመት እድሜ ያላቸው ሰዎችም ሲመርጡ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የመጀመሪያ መራጮችም በመዲናዋ ሴዉል በደስታ ሲመርጡ ታይተዋል።

"መምረጥ መብታችን ነው። ማድረግ ያለብንም ነገር ነው" በማለት የምትናገረው የመጀመሪያ ጊዜ መራጭ ምንም እንኳን ከፕላስቲክ የተሰሩ የእጅ ጓንቶች ለመምረጥ ባይመቹም፤ "ዋናው ደህንነት" ነው ብላለች።

በለይቶ ማቆያ ክሊኒኮች ላይ ሆኖ መምረጥ

ደቡብ ኮሪያ በታሪኳ ውስጥ ምርጫን አራዝማ አታውቅም። በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ በነበረው የኮሪያ ጦርነት እንኳን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት ለባለስልጣኖቹ ዋነኛ ፈተና የነበረው ምናልባት ቫይረሱ ቢዛመትስ የሚል ነበር።

እናም የሙቀት መለኪያው ጣቢያዎቹ ላይ አስገዳጅ የሆነበትም ምክንያት መከላከል ያስችል ዘንድ በሚል ነው።

መራጮች የሙቀት መጠናቸው ከ37.5 ሴንቲግሬድ በላይ ከሆነ ከሌላው መራጭ ተነጥለው በተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲመርጡ ይደረጋሉ።

የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች የምርጫ ውጤታቸውን በፖስታ እንዲልኩ ተጠይቀዋል።

ነገር ግን የኮሮና መካከለኛ ምልክት ለሚያሳዩ ሰዎች ከመኖሪያ ሰፈሮች ራቅ ባለ ሁኔታ አንድ የምርጫ ጣቢያ ተዘጋጅቷል። አንዲት ሴትዮ የሆስፒታል ጋወኗን እንደለበሰችና፣ የፊት ጭምብል አጥልቃ ስትመርጥ ቢቢሲ ተመልክቷል።

"መጀመሪያ መምረጥ አልችልም ብዬ አዝኘ ነበር፤ ነገር ግን ኮሮና ቢይዘንም መምረጥ እንደምንችል ስሰማ በጣም ተደሰትኩ" በማለት ለሮይተርስ ተናግራለች።

ምንም እንኳን ደቡብ ኮሪያ ምርጫ ይካሄድ ብትልም አሁንም የሰአት እላፊ አዋጅ እግዱ እንዳለ ነው። እንዲሁም መራጮች የህዝብ ትራንስፖርት መጠቀም አይችሉም። ወደ ምርጫ ጣቢያዎቹ ሲመጡ በእግራቸው ወይም በራሳቸው መኪና መሆን አለበት። ቤታቸውም ሲመለሱ የጤና ባለሙያዎች ጋር መደወል አለባቸው ካለበለዚያ ለእስር ሊዳረጉ ይችላሉ።

ይህንንም ለማሳለጥ 550 ሺ ሰራተኞች በአገሪቷ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች ተመድበዋል።