ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ትራምፕ ዶ/ር ቴድሮስ በሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት ላይ የገንዘብ እቀባ አደረጉ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኮሮናቫይረስ የሰጠው ምላሽ ቀርፋፋ ነው፤ በአካሄዱም ቻይናን ማዕከል አድርጓል ላሉት የዓለም ጤና ድርጅት አገራቸው የምታበረክተውን የገንዘብ መዋጮ እዲቋረጥ አዘዙ።
ይህም ማለት አሜሪካ ለድርጅቱ በየዓመቱ ለድርጅቱ ትሰጥ የነበረው ገንዘብ እንዲቆም የሚያደርግ ነው ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የትራምፕን ውሳኔ "ጊዜውን ያላገናዘበ እርምጃ" ሲሉ ተችተውታል።
ዶናልድ ትራምፕ ከሳምንታት በፊት ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የሚመሩትን መሥሪያ ቤት ክፉኛ ሲወቅሱ ነበር። በየዓመቱ የሚሰጡትን መዋጮ ለማጤን እንደሚገደዱም ጥቁምታ መስጠታቸው ይታወሳል።
ትራምፕ እንደሚሉት የዓለም ጤና ድርጅት "መሠረታዊ ኃላፊነቱን እንኳ" አልተወጣም። የቫይረሱን የስርጭት ስፋትና አደገኛነት ባላገናዘበ መልኩ እርምጃ አወሳሰዱ የዘገየና ቀርፋፋም ነበር ብለዋል። ከሁሉም በላይ ለቻይና ያደላ ሲሉም ተችተውታል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሁኑ ወቅት ራሳቸውም በአገራቸው ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ለቫይረሱ ባሳዩት ቸልተኝነት ክፉኛ እየተብጠለጠሉ ይገኛሉ። አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ትራምፕ በዓለም ጤና ድርጅት ላይ እየወሰዱ ያሉት እርምጃ የተወሰነ ፋታ ለማግኘትና ትኩረት ለማስቀየር እንደሆነ ይገምታሉ።
ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ለደረሰው ጥፋት ድርጅቱ ተጠያቂ መሆን አለበት" እስከ ማለት ደርሰዋል።
አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት የምትሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ለድርጅቱ ወሳኝና የጠቅላላውን 15 በመቶ የሚይዝ ሲሆን፤ ቻይና በአንጻሩ በፈረንጆቹ 2018/19 ለድርጅቱ ያዋጣቸው ገንዘብ 76 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፤ የአሜሪካ የባለፈው ዓመት መዋጮ 400 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል።
"ድርጅቱ ቫይረሱ ከዉሃን የተነሳ ሰሞን ፈጥኖ እርምጃ ቢወስድ ኖሮ ይህ ሁሉ ቀውስ ባልተፈጠረ ነበር። ከዚያ ይልቅ ቻይና እየወሰደችው የነበረውን እርምጃ ሲያንቆለጳጵስ ነበር" ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩትን ድርጅት ወቅሰዋል፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ።
የቢቢሲ የዋይት ሐውስ ሪፖርት በበኩሉ ፕሬዝዳንቱ ራሳቸው በተመሳሳይ ጊዜ የቻይናን እርምጃ አወሳሰድ ሲያደንቁ ነበር፤ ይህንንም በትዊተር ሰሌዳቸው ጽፈውታል ብሏል።
የአሜሪካንን እርምጃ በተመለከተ የዓለም ጤና ድርጅት መሪ ዶ/ር ቴድሮስ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።