ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ኢኳዶር በአንድ ቀን ከ5ሺህ በላይ ሞት ያስመዘገበችው አገር
በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁት አንዷ የኢኳዶሯ ግዛት ጉዋያ ናት፤ የሞት ጥላም ከቧታል። በአንድ ምሽት አምስት ሺህ ሰዎች ሞተዋል።
በዚህ በያዝነው ወር በሁለት ሳምንት ብቻ 6700 ሰዎች ሞተዋል። በግዛቷ ውስጥ በቀደመው ጊዜ በየወሩ ከሚመዘገበውም የሟች ቁጥር በአምስት ሺ ይበልጣል ተብሏል። ይህም ቁጥር ግዛቲቱን በአገሪቷ ብቻ ሳይሆን በላቲን አሜሪካ ውስጥ ቀዳሚ አድርጓታል።
እነዚህ ሞቶች ግን በኮቪድ-19 ምክንያት ብቻ አይደለም። በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የጤና ሥርዓቷ ፍርስርሱ ሲወጣ በሌሎች በሽታዎች በጠና ታመው የነበሩ ህሙማን የጤና ማዕከላትን እርዳታ ሳያገኙ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ጉያኩል፤ የሞት ከተማ
በጉዋያ ግዛት ያለችውና የኢኳዶሯ ትልቅ ከተማ ጉያኩል ለቅሶ፣ ሃዘን፣ ግራ መጋባት ወሯታል።
"የሞቱ ሰዎችን በመኪኖች፣ በአምቡላንስ፣ በቤታቸቸው፣ በየጎዳናው፣ በየቦታው ተረፍርፈው አግኝተናል" ይላሉ የቀብር አስፈፃሚዋ ካቲ መካ።
"ሆስፒታል በነበረ የአልጋ እጥረት ምክንያት ተኝተው መታከም አልቻሉም። የግል ክሊኒኮችም ወጪ ከፍተኛ ነው። ሁሉም ሰው መክፈል ይችላል ማለት አይደለም" ይላሉ።
2.5 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ግዛት ያሉ መካነ መቃብሮችም ሆነ የቀብር አስፈፃሚዎች አስከሬኖቹን የመቅበር ሥራ ከአቅማቸው በላይ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ቫይረሱ ይይዘኛል የሚልም ስጋት አለ።
ተስፋ የቆረጡና የቤተሰቦቻቸውን አስከሬን ምን ውስጥ እንደሚያስገቡት ጭንቅ ጥብብ ያላቸው በየቤታቸው በር ላይ አስቀምጠዋቸዋል። አስከሬኖች በሚያሰቅቅ ሁኔታ ከሞቱበት እልጋ ለቀናት ያህል ተጣብቀው ይገኛሉ።
ለከተማዋ ታይቶ ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ ይህን ያህል ሰው በመሞቱ የመካነ መቃብር እጥረትም አጋጥሟል። ወደ ጎረቤት ከተሞችም አስከሬኖች ለቀብር ተልከዋል።
ቦታ ብቻ ሳይሆን የአስከሬን ሳጥንም ችግር በማጋጠሙ በከርቶን ውስጥ አስከሬኖቹን ተደርገው ለመቅበር ተገደዋል። እስረኞችም ጣውላ በመጥረብ የአስከሬን ሳጥን እየሰሩ ነው።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሌኒን ሞሬኖ አገራቸው ያጋጠማትን ድንገተኛ የጤና ቀውስ ሳትወጣ ቀርታለች ብለዋል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መንግሥት በአጠቃላይ በአገሪቱ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 400 ነው እያለ ነበር።
ነገር ግን በመንግሥት ስር ያለው የኮሮናቫይረሰ ጥምር ግብረ ኃይል ሁሉንም መረጃዎች ሲሰበስብ መንግሥት ከሚለው ጋር በፍፁም ተቃራኒና፤ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ነበር።
"ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከመካነ መቃብሮች ያገኘነው መረጃ የሚያሳየው 6ሺ703 ሰዎች በሁለት ሳምንት መሞታቸውን ነው" ይላሉ ጆርጅ ዋትድ የጥምሩ ግብረ ኃይል ኃላፊ።
"ቀድሞ በከተማዋ በየወሩ የሚሞተው ሰው ቁጥሩ 2 ሺህ ነበር። ስለዚህ 5700 ሰዎች ከነበረው በተጨማሪ ሞተዋል" ይላሉ።
ሁሉም የሞቱት በኮሮናቫይረስ አይደለም፤ በልብ ድካም፣ በኩላሊት ህመም እንዲሁም በሌሎች በሽታዎች የሞቱ ሰዎች አሉ።
ይፋዊ የሆነው ቁጥርና መሬት ላይ ያለው እውነታ ክፍተት አሰቃቂ ሐቆችን ፍንትው አድርጎ አውጥቷል።
በተጨማሪም ይሄንን ያህል ቁጥር ያለው ሰው መሞቱም በርካታ ጥያቄዎችን አጭሯል። በተለያዩ ላቲን አሜሪካ አገራትስ እንዲሁም የጤና ሥርዓታቸው ደካማ በሆነባቸው አገራት እንዲህ አይነት አሰቃቂ ክስተት ይከሰት ይሆን? የሚለውም አስደንጋጭ ሆኗል።
የቫይረሱ መነሻ የሆነችው ዉሃንም ቀደም ሲል በበሽታው ሞተውብኛል ያለቻቸው ሰዎች አሃዝ ላይ 1290 በመጨመር በ50 በመቶ ከፍ ብሏል።
የከተማዋ ባለስልጣናት እንዳሉት ይህ አሃዝ ሊጨምር የቻለው አዲስ በተገኙ ቁጥሮችና ከሆስፒታል ውጪ የሞቱ ሰዎችን በማካተቱ ነው።
በቫይረሱ ክፉኛ በተጠቃችበት ስፔንም በብሔራዊ ደረጃ የሚነገሩ አሃዞችና ከተለያዩ አካባቢዎች የሚሰብስቡ መረጃዎች ላይ ከፍተኛ ልዩነት አለ።
"የኢኳዶር የጤና ሥርዓት ደካማ ነው። መንግሥት ትኩረት ያልሰጠበት ዘርፍ ነው" በማለት ዶክተር ካርሎስ ማውይን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኢኳዶር ላይም ያለውን የኮቪድ-19 ቀውስንም ማዕበል ብለውታል።
"በደከመ የጤና ሥርዓት ይህንን ያህል ቁጥር ያለው በሽተኛ ሲመጣ፤ የአገሪቱን የጤና ሥርዓት አሽመድምዶታል። የፅኑ ህሙማን ህክምናንም አፈራርሶታል" ብለዋል።
ኢኳዶር ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሰዓት እላፊን ማወጅ እንዲሁም በርካታ ህመምተኞችን እመረምራለሁ ብትልም፤ የሚወዷቸው ሰዎች ከአይናቸው ለተነጠቁባቸው የግዛቷ ነዋሪዎች ይህ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም እየተባለ ነው።