ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአንድ ሩሲያዊ ቢሊየነር ሚስት ምስቅልቅል ታሪክ
አሌክሳንድራ ቶልስቶይ ምን ይወጣላታል። ቆንጆ ናት . . . ሰልካካ አፍንጫ፣ መቃ አንገት. . .
እንግሊዛዊት ናት። እንግሊዝኛ አስተማሪም ነበረች። ከዕለታት አንድ ቀን ስለቷ ሰመረ። ቢሊየነር አገባች። ሩሲያዊ ቢሊየነር።
ይህ እጅግ የናጠጠ ሩሲያዊ ሰርጌይ ፑጋቼቭ ይባላል። እንግሊዝኛውን ማሻሻል ይፈልግ ነበር። በአጋጣሚ ወይዘሪት አሌክሳንድራ ቶልስቶይ አስተማሪው ሆና ተቀጠረች።
በእንግሊዝኛ ልምምድ መሀል ታዲያ መላመድ መጣ። በቋንቋ ጥናት መሀል መጠናናት መጣ። ቀስ በቀስ ትወደው ጀመር፤ ቀስ በቀስ በፍቅሩ ከነፈች። በመጨረሻም ወደደችው፤ ወደዳት። ተጋቡ።
ነገሮች መልካቸውን ለመለወጥ ግን ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም።
የቢሊየነር ትዳር ውስጥ ንፋስ ይገባል?
ታሪኩ የሚጀምረው የዛሬ 5 ዓመት በሎንዶን ከተማ ነው።
መጀመርያ በሎንዶን የዲታዎች ሰፈር ቼልሲ ውሰጥ መኖር ጀመሩ። ሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጣ ቤተ መንግሥት የመሰለ ቤት ገዙ። ከሦስት ልጆቻቸው ጋር ገቡበት።
"አንዳች የጎደለብን ነገር አልነበረም" ትላለች አሌክሳ።
"ለሁለታችንም የግል ረዳቶች፣ የቤት ሠራተኞች፣ የግቢያችን ውበት ጠባቂዎች፣ የልጆቻችን ተንከባካቢዎች፣ የግል ጠባቂዎች፣ ጤናችንን የሚከታተሉ ሐኪሞች፣ ሾፌሮች፣ ፈረንሳይኛ ቋንቋ አስተማሪ. . . ብቻ ሁሉም ዓይነት ረዳቶች ነበሩን።"
አሌክሳ ለቢቢሲ ዘጋቢ ቀድሞ ይኖሩበት የነበረውን ቤት እያስጎኘች ነው ይህን የምትናገረው።
"ወደዚህ ቤታችን የተዘዋወርነው የመጀመሪያ ልጄን እንደወለድኩ ነበር፤ ቀጥለን ደግሞ ይሄን የጎረቤታችን ቤት ገዛን። ቀጥለን ደግሞ ያንን፣ ቀጥለን ደግሞ ያኛውን. . ."
አሌክሳና ሰርጌይ ያዩትን፣ ያማራቸውን ሁሉ ለመግዛት የሚያበቃ ሀብት ነበራቸው። የወደዱትን የእነርሱ ለማድረግ እንደተቀረው ዜጋ ሁለት ጊዜ ማሰብ አይጠበቅባቸውም።
የደራሲው ሊዮ ቶልስቶይ ዘመድ
የአሌክሳ ቅምጥል ሕይወት ቢሊየነሩን ሰርጌይን ስታገባ የጀመረ አይደለም። ቢያንስ በችጋር አላደገችም። ልጅነቷ ይህ ጎደለው የሚባል አልነበረም። እርግጥ ነው የናጠጡ ሀብታሞች አልነበሩም፡፡ ሆኖም ተብቃቅተው ነው የኖሩት ማለት ይቻላል።
አባቷ የዕውቁ ሩሲያዊ ደራሲ የሊዮ ቶልስቶይ የሩቅ ዘመድ ነበር። የተማረችው ውድ በሚባል ትምህርት ቤት ነው፤ በኋላ የቤት አሻሻጭ ሆነች። እሱንም እርግፍ አድርጋ ትታ የጉዞ ወኪል ከፈተች።
በኋላ ግን እንግሊዝን ትታ፣ ሥራዋን ሁሉ ታትታ ወደ ሩሲያ አቀናች። ትንሽዬ የቱሪዝም አስጎብኚ ድርጅት ከፈተች። በጉርድሚኒስታን እና ኪርጊስታን ጎብኚዎችን ይዛ ፈረስ እያስጋለበች ገጠሩን ክፍል ታስጎበኝ ጀመር።
ይህን ሥራ ስትሰራ አንድ የኡዝቤክ ኮሳክ ተወላጅ ሰው አግብታ ነበር። ትዳራቸው ግን ብዙም አልሰመረም። ሁሉን ትታ እንግሊዝኛ ወደ ማስተማሩ ተመለሰች።
በዚህ መሀል ነበር ቢሊየነሩን ሰርጌይን ያገኘችው።
"ገበያ የምወጣው በግል አውሮፕላኔ ነው"
ሰርጌይን ያገኘሁ ዕለት ደስታዬ ወደር አልነበረመው። በፍቅሩ ሙትት አልኩኝ። ዓለሜ ሁሉ ሰርጌይ ሆነ፤ እሱን ከማግኘቴ በፊት እንደዚህ ዓይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር" ትላለች አሌክሳንድራ።
በመጀርያዎቹ ጊዜያት እሱም እንደዚያ ነበር የሚለው፤ ሕይወታችን አልጋ በአልጋ ነበር።
አንድ ቦታ መኖር ለእኛ ከባድ ነበር። ስለዚህ በፓሪስ፣ ሞስኮና ሎንዶን ቤቶቻችን እያፈራረቅን እንኖራለን።
"በእውነቱ ባሌ ሰርጌይ ከተማ ውስጥ በሌለ ሰዓት፣ ወይም ሞስኮ በሥራ ሲወጠር ክሬዲት ካርዱን ይሰጠኝና ገበያ እወጣለሁ፤ መገዛዛት ሲያምረኝ የግል ጀቴን አስነስቼ ወዳማረኝ አገር መብረር ነው. . . ።"
አሌክሳ የሀብታቸውን መንዛዛት ስታስረዳ. . .
"ብዙ ቤቶች ስለነበሩን አንድ ቤት ውስጥ ብዙ ጊዜ ለማሳለፍ አልታደልንም። ለምሳሌ የ12 ሚሊዮን ፓውንዱ ቤት በባተርሲ ሎንዶን፣ ሌላ ቤት በሄልፎልሻየር፣ ሌላ ቤት በፓሪስ. . . ደግሞ በካሪቢያን የሚገኘው የ40 ሚሊዮን ፓውንድ የባሕር ዳርቻ ቪላ. . . ብቻ ያማረን ቤት ውስጥ ነበር የምንኖረው። እንደ ወቅቱና አየሩ ጠባይ።"
የአሌክሳንድራና ሰርጌይ ሕይወት ሕልም ነበር የሚመስለው። በድንገት ታዲያ ነገሮች መለዋወጥ ጀመሩ። ሩሲያ ውስጥ ፖለቲካው ተቀየረ።
ቆፍጣናው ፑቲን የእርሷን ባል ጨምሮ በአንዳንድ የሩሲያ ቢሊየነሮች ላይ ፊቱን አዞረ።
ሰርጌይ ከዚያ በኋላ የሆነውን እንዲህ ይናገራል. . .
'የፑቲን ሳምሶናይት'
ሰርጌይ ፒካቼቭ ብዙዎች የሚያውቁት የፑቲን የገንዘብ ሳምሶናይት በሚል ተቀጽላ ነው። ያለ ምክንያት አይደለም። አንድ ወቅት ላይ ለፑቲን መንግሥት ገንዘብ አበድሮ ያውቃል።
ሰርጌይ መጀመርያ ወደ 15 ቢሊዮን ዶላር ሀብት ያካበተው ከኮሚኒስቷ ሩሲያ በኋላ በተፈጠረ ቢዝነስ ነው።
የከሰል ማዕድን አለው፤ የመርከብ ጋራዥም እንዲሁ። ከሩሲያ የግል ባንኮች ውስጥ ትልቁ የእሱ ነበር። ታዲያ የሰርጌይ ፒካቼቭ ሀብት ይህ ብቻ ነው? አይደለም። ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሌሎች ንግዶች አሉት።
ሰርጌይ ቪላድሚር ፑቲንን "ከእኔ የተሻለ የሚቀርበው ሰው አልነበረም" ይላል። "የዚህ ማሳያም ለምሳሌ አውዳመት አብረን ነበር የምናሳልፈው፤ ሁልጊዜም።"
የሆነ ወቅት ላይ ፑቲንና መንግሥታቸው ገንዘብ ቸገራቸው፤ ሰርጌይ ፒካቼቭ ለፑቲን ገንዘብ አበደረ። ከዚህ በኋላ ነበር "የፑቲን ሳምሶናይት" የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ብለናል።
ሆኖም በዚህ ሁሉ ቀርርባቸው ውስጥ አንድ ፑቲን ያልወደዱለት ነገር ነበር፤ ሚስቱን አሌክሳንድራን።
"ፑቲን አሌክሳንድራ ቶልስቶይን አልወደዳትም። መጀመርያ ላገባት ነው ብዬ ስነግረው በጣም ነው የተገረመው። 'ምን ነካህ? ለምን እሷን መረጥክ? ለዚያውም እንግሊዛዊት. . .!? ሩሲያ ውስጥ 140 ሚሊዮን ሰው እያለልህ?' ብሎ ተቆጣኝ።"
ሰርጌይንና ሰርጌይን የመሳሰሉ የራሺያ የገዢ መደብ ባለጸጎች (ኦሊጋርክስ) ላይ ፑቲን ድንገት ተነሱባቸው። ምክንያታቸው በትክክል ምን እንደሆነ እርሳቸውና ፈጣሪ ነው የሚያውቀው።
ብቻ በጎርጎሮሲያኑ 2006 ሩሲያ አዲስ ሕግ አወጣች፤ ማንኛውንም በውጭ የሚኖርና ለእናት አገሩ ሩሲያ ጠላት የሆነ ባለጸጋ በተገኘበት እርምጃ ይወሰድበት።
የፑቲን ሰዎች በሰርጌይ ፒካቼቭ ላይ የዘመቱት ከዚህ በኋላ ነበር።
በ2008 የሰርጌይ ባንክ የገንዘብ ችግር ገጠመው። የሩሲያ መንግሥት አንድ ቢሊየን ዶላር ብድር ሰጥቶ ከመውደቅ ታደገው ተባለ። ያም ሆኖ ከ2 ዓመት በኋላ ባንኩ ኪሳራ አወጀ።
ሰርጌይ እንደሚለው ባንኩን ቀደም ብሎ ሽጦታል። ሩሲያ ግን በፍጹም አለች። እንዲያውም ላደረስከው ኪሳራ ትጠየቃለህ አለችው። ያበደርንህን አንድ ቢሊየን ዶላር መልስ አለችው. . . ። ተፋረሱ።
የሩሲያ ፍርድ ቤት ለባንኩ መንኮታኮት ተጠያቂው ፑካቼቭ ነው ሲል ወሰነ። ሰርጌይ ፑካቼቭ ከዚህ በኋላ አገር ለቆ ተሰደደ።
ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ሰርጌይን ከምሽቶች በአንዱ የሩሲያ ዲፖዚት ኢንሹራንስ ኤጀንሲ ሰዎች "እዳ አለብህ" አሉት።
"የምን እዳ?" አላቸው።
"ያንተ ባንክ እኛን ለኪሳራ ዳርጎናልና ብር እንፈልጋለን" አሉት።
ይህ ትንኮሳ ጋብ እያለ ቀጠለ። ስለሚመጣው ነገር ምልክት ነበር. . .
"በሌላ ቀን ደግሞ ሬስቶራንት ለእራት ቀጠሩኝና እራት ከበላን በኋላ 350 ሚሊዮን ዶላር በአካውንታችን አስገባ አሉኝ፤ ካልሆነ አንተና ቤተሰብህን እንገድላለን አሉኝ።"
"ይህ እንደማይሆን ስነግራቸው 'የልጅህን ጣቶች ቆርጠን በፖስታ ቤት እንልክልሃለን' አሉኝ።"
ኤጀንሲው ግን ይህን ስለማለቱ ይክዳል፤ ሆኖም ሰርጌይ ፑካቼቭ የተጠየቀውን ለመክፈል አልፈቀደም። ከአገር መሰደድን መረጠ፤ ወደ እንግሊዝ።
ሰርጌይ በስደት በነበረበት ወቅት የሩሲያ ጠላቶች የተባሉ ሁሉ በየቦታው እንደቅጠል መርገፍ ጀመሩ።
እሱም በእንግሊዝ ሳለ ክስ ከፈቱበት፤ አብዛኛው ሀብቱ እንዳይንቀሳቀስ አደረጉ፤ ፓስፖርቱ እንዲቀማ አደረጉ. . . አንድ ቢሊየነር ዶላር ከአካውንቱ ማሸሽ ቻሉ. . .ነገሮች አላምርህ ሲሉት ታዲያ ሰርጌይ ወደ ፈረንሳይ ተሰደደ።
"የእናት ሩሲሺያ ጠላቶች በተገኙበት እርምጃ ይወሰድባቸው"
በ2012 ከሩሲያ ቢሊየነሮች አንዱ የነበረውና የሩሲያን ምስጢር አዝረክርኳል ተብሎ የሚታመነው አሌክሳንደር ፐረፒልቺኒ በእንግሊዝ ደቡብ ምሥራቅ ሎንዶን ከቤቱ ዱብ ዱብ ሊል ደጅ በወጣበት ተገድሎ፣ ተጥሎ ተገኘ።
በ2013 የፑቲን ተቀናቃኝ ቦሪስ ቤሬቮስኪም እንዲሁ እንግሊዝ በአስኮት አካባቢ ቤቱ ውስጥ ሳለ ተገድሎ ተገኘ።
በ2015 የሩሲያ ተቃዋሚ የነበረው ቦሪስ ኔምሶቭ በሞስኮ አደባባይ ላይ ተገደለ።
ሰርጌይም ይህ እጣ እንደሚጠብቀው አላጣውም። ለዚህም ነው ከእንግሊዝ ወደ ደቡብ ፈረንሳይ የሸሸው።
የሽሽት ሕይወትና የትዳር መፍረስ
አሌክሳንድራ ባሏ ሰርጌይ በሽሽት ላይ መሆኑ ሕይወታቸውን እንዳመሰቃቀለው ትናገራለች።
"ባሌ ሰርጌይ ሁልጊዜም በሽሽት ነው የሚያሳልፈው፤ እኔና ልጆቼም ክትትል አለብን።"
ነገሮች ለእርሷና ለልጆቿ መልካም አልነበሩም። ይህ ሁኔታ በሚያስቀናው ትዳራቸው ላይ ንፋስ እንዲገባ አደረገ።
በተለይ ከ2016 ጀምሮ ነገሮች መልካቸውን ለወጡ።
"ፈረንሳይ በሚገኘው ቤታችን አብረን ከልጆቻችን ጋር በቋሚነት እንኑር ሲለኝ አቅማማሁ፤ ምክንያቱም ተደብቄ መኖር አልፈልግም፣ እስከመቼ?"
". . . አንድ ቀን ታዲያ ፈረንሳይ ካለው ቤት ሳለን ባሌ ሰርጌይ በጥፊ አላጋኝ። ልጆቹን ደግሞ ከእኔ ለያይቶ አንድ ክፍል ውስጥ አስገብቶ ቆለፈባቸው። ፓስፖርቴን የሆነ ቦታ ወስዶ ደበቀው።. . ."
"…ያን ቀን በቃ ከእሱ ጋር ያለኝ ነገር እንዳበቃ ተሰማኝ። ከዚህ በኋላ በጸደይ ወር 2016 በድንገት ከደቡብ ፈረንሳይ ቤታችን ልጆቼን ይዤ ወደ እንግሊዝ አመለጥኩ። እስከወዲያኛው ላልመለስ. . . "
ከቢሊየነርነት ማማ መውረድ
ከዚያ ጊዜ በኋላ ሰርጌይ እኔም ልጆቼንም በገንዘብ ይቀጣን ጀመር። እጄ ላይ ምንም አልነበረም. . .
"ሰዎች ሲያገኙኝ ሕይወትሽ አባጣ ጎርባጣ የለበት፤ እንዴት የሚያስቀና ሕይወት ነው ያለሽ ይሉኛል፤ ውስጤን አያውቁልኝም" ስትል እንባ እየተናነቃት ለቢቢሲ ተናግራለች፤ አሌክሳ።
"የሚያስቀና ሕይወት ማለት በፍቅር አብሮ መኖር ነው፤ ያለ ፍርሃት፤ ደኅንነት እየተሰማ. . . እንጂ የገንዘብ መኖር ብቻውን የተሻለ ሕይወት አያኖርም. . . "
አሌክሳ እንደምትለው ከፈረንሳይ ከሰርጌይ ካመለጠች ወዲህ ከልጆቿ ጋር የሚኖሩበትን የቤተሰብ ቤት የሩሲያ መንግሥት በሕግ አሳግዶት ለገበያ ሊያቀርበው በሂደት ላይ ነበር።
"ለአንድ ዓመት በነጻ እንድትኖሪ ከፈለግሽ አስገዳጅ ስምምነት ፈርሚ አሉኝ. . . ። ወደ ሌላ ክስ አልሄድም ብለሽ ፈርሚ አለበለዚያ ባዶሽን ትቀሪያለሽ ነው ያሉኝ።"
የሩሲያና የእንግሊዝ ግንኙነት መሻከር
በ2018 የሩሲያ ድርብ ሰላይ የነበረው ሰርጌይ ስክሪፓል እንግሊዝ ውስጥ ተመረዘ።
ከዚህ በኋላ የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ቢሮ ተያያዥ ጉዳዮችን እንዲመረምር ታዘዘ። 14 ተመሳሳይ ግድያዎችን ሲያጣራ ከብዙዎቹ ጀርባ የሩሲያ ሰላዮች እጅ እንዳለበት አረጋገጠ።
በዚህን ጊዜ የእንግሊዝና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በእጅጉ ሻከረ።
"ኪሴ ላይ የቀረችኝ 70 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ናት" ሰርጌይ
ሰርጌይ ከዚያ ሁሉ ቢሊዮን ዶላር በኋላ የፑቲን መንግሥት ፊቱን ሲያዞርበት አግኝቶ ያጣ ሆነ።
አሁን ደቡብ ፈረንሳይ በሚገኘው ቤቱ ነው የሚኖረው። ብቻውን። 'ሕይወቴን ያመሰቃቀሉት የፑቲን ሰዎች ናቸው' ይላል።
"ልጆቼን እወዳቸዋለሁ፤ አንድ ቀን ልጆቼ ከአባታቸው ጋር ይሆናሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ይላል።
አሁን የሰርጌይ ልጆች የሚኖሩት ከአሌክሳ ጋር በኦክስፎርድሻየር በትንሽ ቤት ውስጥ ነው። ከ2016 ጀምሮ አባታቸውን አይተውት አያውቁም።
"አንድ ቀን ነገሮች መልክ ሲይዙ ታገኙታላችሁ፤ ወይም ትልቅ ስትሆኑ ሄዳችሁ ትጎበኙታላችሁ እላቸዋለው" ትላለች እናታቸው አሌክሳንድራ።
አሁን አሌክሳንድራ ወደ ድሮው ማንነቷ ተመልሳለች። ከቢሊየነርነቷ ወርዳ በኪርጊስታን ፈረስ እየጋለበች ቱሪስቶችን ታስጎበኛለች።
"ሩሲያን እወዳታለሁ፤ በሚገርም ሁኔታ እኔ ከሩሲያ ጋር ያለኝ ግንኙነት ከሰርጌይ ጋር ካለኝ ግንኙነት የተሻለ ነው" ትላለች።
ከቅንጡ ሕይወቷ ለአንዴና ለመጨረሻ ተፋታለች።
"እንዲያውም ያንን የሕይወቴን ክፍል የምጠላው ይመስለኛል፤ ቅንጡ ነገሮችን ሳይ ያ የማልወደውን ሕይወቴን ነው የሚያስታውሱኝ" ትላለች።
"ከፊቴ ገና ብዙ ሕይወት አለ፤ ወደምወዳቸው ነገሮች ለመመለስ እችላለሁ፤ ውስጤን ደስ የሚያሰኙት እንደዚያ ያሉ ነገሮች ናቸው።"
"የቀድሞ ባሌ፤ ቢሊየነሩ ባሌ ከሱና ከገንዘቡ ተጣብቄ የምኖር ይመስለው ነበር፤ ተሳስቷል።"