ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመሰለል የምትከሰሰው ሩሲያ 600 የሚጠጉ የውጪ ሀገራት 'የስለላ' ሰራተኞችን ቀነሰች
ፕሬዝዳንት ፑቲን የውጭ ሃገራት የስለላ ስራ በሩሲያ ላይ እየተጠናከረ በመምጣቱ ምክንያት በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2018 ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሃገራት የስለላ ሰራተኞች መታገዳቸውን አስታውቀዋል።
ዝርዝር መረጃ ከመስጠት የተቆጠቡት ፕሬዝዳንቱ 129 ቋሚ ሰራተኞችና 465 ተወካይ የውጭ ልዩ የስለላ አገልግሎት ሰራተኞች ታግደዋል ብለዋል።
ሩሲያ የሌሎች ሃገራትን የስለላ ሰራተኞች ብታግድም የራሷ የስለላ ሰራተኞች ራሳቸው የተለያዩ ሴራዎችን በመጠንሰስ ይከሰሳሉ። ለምሳሌ የቀድሞውን የስለላ ወኪል ሰርጊ ስክሪፓል ለመመረዝ ማሴራቸው ይነገራል።
የአውሮፓ ህብረትና እንግሊዝ ባለፈው አመት የስከሪፓል ጥቃትን ያቀነባበረቸው ሩሲያ ናት ማለታቸውን ተከትሎ 25 ሃገራት የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከሃገራቸው አስወጥተው ነበር።
አሁን ሩሲያ በወሰደችው ርምጃ ሆላንድ ፣ ቼክ ሪፖብሊክና ስዊድን የስለላ ሰራተኞቻቸው የታገዱባቸው ሃገራት ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ ሩሲያ በምርጫ ጣልቃ በመግባትም በምዕራባዊያን ዘንድ ትከሰሳለች።
በስም ሩሲያ ብለው ባይጠቅሱም የአውሮፓ ህብረት ካውንስል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ተስክ ባለፈው ማክሰኞ "ጸረ የአውሮፓ ህብረት" የሆኑ አካላት ግንቦት ላይ በሚካሄደው የህብረቱ የምክር ቤት ምርጫ ጣልቃ ለመግባት እየሰሩ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በመግለጫቸው "የወጭ የስለላ አገልግሎቶች በሩሲያ ላይ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጅ ፍላጎታቸው እየጨመረ ነው በመሆኑ ለሩሲያ ይበጃል ያልነውን የመፍትሔ ርምጃ ወስደናል'' ብለዋል።
እንደዚህ አይነት ተግባራት በሩሲያ እየተለመደ መጥቷል። በየአመቱ ፕሬዝዳንቱ የፌደራሉን የደህንነት ተቋም ይጎበኛሉ።
በዚህ ጉብኝታቸውም ሩሲያ ምን ያክል የውጭ የደህንነት ሰራተኞችን እየተከታተለች እንደሆነ ከአመት አመት ያለውን ንጽጽር ይገልጻሉ።
ከአራት አመት በፊት 52 ቋሚ ሰራተኞችንና 290 የውጭ ወኪል የስለላ ሰራተኞችን እንደሚቀንሱ ቢናገሩም አሁን ላይ የተመዘገበው ቁጥር ግን ከተባለው ጋር ሲነጻጸር የተጋነነ ነው። 129 ቋሚና 465 የውጪ ወኪል ሰራተኞች ተቀንሰዋል።