አሜሪካዊቷ ሴናተር ማርታ ማክሳሊ በአየር ኃይል ባለስልጣን እንደተደፈሩ ተናገሩ

አሜሪካዊቷ ሴናተር ለስራ ባልደረቦቿ እንደተናገሩት አየር ኃይል በነበሩበት ወቅት በከፍተኛ ጦር መኮንን እንደተደፈሩ ተናግረዋል።

ሴናተር ማርታ ማክ ሳሊ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት የጦር አውሮፕላን አብራሪ ሲሆኑ በሰራዊቱ ውስጥ ስላለው ወሲባዊ ጥቃትን በተመለከተ በነበረ ስብሰባ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሪፐብሊካን አባል የሆኑት ሴናተሯ በተደፈሩበት ወቅት መሸማቀቅ፣ ግራ መጋባትና በአጠቃላይ የመረበሽ ስሜት ስለደረሰባቸው ለማንም ሳይናገሩ ዋጥ አድርገው እንደቆዩ ተናግረዋል።

በአሜሪካ ጦር ውስጥ የሚፈፀሙ ፆታዊ ቃቶች የህዝብ ጆሮ የማያገኙ ሲሆን፤ ከሁለት አመት በፊት ያለውም መረጃ እንደሚያሳየው 10% ብቻ ናቸው ይፋ የወጡት።

ሴናተሯ ምክር ቤቱ ላቋቋመው ኮሚቴ ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት "ለረዥም አመታት ዝም ብየ ቆይቻለሁ" ብለዋል።

"ነገር ግን ጦሩ በተለያዩ ቅሌቶች ከመዘፈቁ ጋር ተያይዞና ለሚመጡት ጥቃቶችም የሚሰጡት ምላሽ እርባና የሌለው በመሆኑ እኔም በዚህ ጥቃት አልፌ የተረፍኩ መሆኔን መንገር ፈለግኩ" ብለዋል።

በአሜሪካ የአየር ኃይል አባልነት ለ26 አመታት ያገለገሉት ሴናተሯ ብዙ ጥቃት እንደደረሰባቸው ግለሰቦች በሀዘን ከቦታው እንደለቀቁ ይናገራሉ። " ብናገር ሊደርስ የሚችለውን ሰቆቃ ሳስበው ፤ ስርአቱ በተደጋጋሚ እንደደፈረኝ ይሰማኛል" ብለዋል።

ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት ኮሎኔል ማዕረግነት የደረሱት በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ጊዜ ተመርጠዋል። በባለፈው አመትም የምክር ቤቱን ምርጫ አሸንፈዋል።

ሴናተሯ 17 አመታቸውም ላይ ፆታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ለዋል ስትሪት ጆርናል ተናግረው ነበር።

በጥር ወር ላይም ጆኒ ኧርነስት የተባሉ በሰራዊቱ ውስጥ ለብዙ ዘመናት ያገለገሉ ሴናተር እንደተደፈሩ ተናግረው፤ በወቅቱ ለፖሊስም እንዳልተናገሩ ገልጸዋል።