የሐጅ ተጓዦች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እስኪለይለት ታገሱ ተባሉ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ዓመታዊው የሙስሊሞች መንፈሳዊ ጉዞ (ሐጅ) ዘንድሮ የመሆኑ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። ሳኡድ አረቢያ "እባካችሁ ተረጋጉ፤ ነገሮች እስኪለይላቸው" ብላለች በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞችን።
የሐጅ ጉዳዮች ሚኒስትር ሙሐመድ ባንቴን ባስተላለፉት መልዕክት አገራቸው ሳኡዲ ከመላው ዓለም ለሚመጡ መንፈሳዊ ተጓዦች ደኅንነት ትጨነቃለች፤ ስለዚህም ነገሮች እስኪለይላቸው የጉዞ እቅድ እንዳታወጡ እንመክራለን ብለዋል።
በቀጣይ ሐምሌና ነሐሴ ወራት በትንሹ 2 ሚሊዮን የሐጂ መንፈሳዊ ተጓዦች ወደ መካና መዲና ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
ከአምስቱ የእስልምና መሰረቶች አንዱ የሐጅ ጉዞ ሲሆን ማንኛውም የእስልምና ተከታይ አቅሙ ሲፈቅድ ቢያንስ አንድ ጊዜ በሕይወት ዘመኑ የሐጅ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲሳተፍ ይጠበቃል።
በብዛት ከሐጅ ቀደም ብሎ ይደረግ የነበረው የኡምራ ሥነ ሥርዓት ዘንድሮ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል። ሆኖም ኡምራ በማንኛውም የዓመቱ ወቅት የሚካሄድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው።
በአሁኑ ወቅት ከመንፈሳዊ ተጓዦች ውጭም ቢሆን መካና መዲና እንዲሁም ዋና ከተማዋ ሪያድ ድንበሮቻቸውን ዘግተዋል።
ኮቪድ -19 በሳኡዲ አረቢያ 1563 ሰዎች ማጥቃቱ የተረጋገጠ ሲሆን 10 ሰዎችንም ገድሏል።
"ሳኡዲ በሁሉም ጊዜና ሁኔታ አማኞችን ትቀበላለች፤ አሁን በመላው ዓለም በሆነው ነገር የፈጣሪን ምሕረት እንጠይቃለን፤ እንግዶቻችንን ደኅንነት ለመጠበቅ ስንል ለጊዜው የጉዞ እቅድ እንዳያደርጉ አደራ እንላለን" ብለዋል ሼክ ባንተን።
ሚኒስትሩ ጨምረው እንዳሉት ለኡምራ ከኮሮናቫይረስ ከስተት በፊት ወደ አገሪቱ በገቡ መንፈሳዊ ተጓዦችና እነርሱን ባስተናገዱ ሆቴሎች ላይ ጽዳት እየተደረገ ነው። የተጠረጠሩ እንግዶቹንም ወደ ለይቶ ማቆያ የማስገባት ተግባርም ተካሄዷል።
ሚኒስትሩ ለኡምራ ቪዛ ገዝተው የነበሩ አማኞች ገንዘባቸው እንደሚመለስላቸው አረጋግጠዋል።














