ኮሮናቫይረስ ቤላሩስ፡ በኮቪድ-19 ያልተሸበረችው ብቸኛዋ አውሮፓዊት አገር

ቅዳሜ ዕለት ጨዋታ ለማየት ስታዲየም ከነበሩ ተመልካቾች በከፊል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቅዳሜ ዕለት ጨዋታ ለማየት ስታዲየም ከነበሩ ተመልካቾች በከፊል

አሁን አውሮፓ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማዕከል ነች። ነገር ግን አውሮፓ ውስጥ ሆና ባላስልጣናቷ በአሁኑ ጊዜ ዓለምን እኣስጨነቀ ስላለው የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝ ምንም አይነት የተለየ ማስጠንቀቂያም ሆነ ትዕዛዝ የማይሰጡባት አገር አለች።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ቤላሩስ ከሌሎች የአውሮፓ አገራትም ሆነ ከጎረቤቶቿ ሩሲያና ዩክሬን የተለየ መንገድ እየተከተለች ነው።

ጎረቤት ዩክሬን በመዲናዋ ኪየቭና በሌሎች ግዛቶቿ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች። ሩሲያም ትምህርት ቤቶችን ዘግታለች፣ ብዙ ሰው የሚያሰባስቡ ዝግጅቶችን ሰርዛለች። በተጨማሪም ሁሉንም በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚደረጉ በረራዎችን አቁማለች።

በቤላሩስ ግን በብዙ መንገድ ሕይወት በትናንቱ መንገድ እየቀጠለ ነው። ቤላሮስ ምንም እንኳ 94 ዜጎቿ በቫይረሱ ቢያዙም [ሞት አልተመዘገበም እስከ ትናንት ድረስ] ድንበሮቿ ክፍት ናቸው፣ ሰዎች ወደ ሥራ ይሄዳሉ፣ እንዲያውም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ 6 ታላላቅ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ቤላሩስ ውስጥ ተደርገዋል።

'አትሸበሩ'

የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አገራቸው የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት ምንም አይነት ቅድመ ጥንቃቄ እንደማያስፈልጋት ገልጸዋል።

"የሚያጋጥም ነገር ነው። ዋናው ነገር ግን አለመደንገጥ ነው " ብለዋል ባለፈው ማክሰኞ ሚኒስክ ውስጥ ከቻይናው አምባሳደር ጋር በተገናኙበት ወቅት።

ቤላሮስ ቲያትርን፣ ሲኒማን ወይም ሌሎች ሕዝባዊ መሰባሰቦችን አልከለከለችም።

ቤላሩስ በዓለም ላይ ካሉ አገራት መካከል የእግር ኳስ ውድድሯን ያላቋረጠች ብቸኛዋ አገርም ናት።

የቤላሩስ እግር ኳስ የውስጥ ሊግ እንደቀጠለ ሲሆን ተመልካቾችን ሰብስቦ ከማዝናናት በተጨማሪ ለጎረቤት ሩሲያዊያን ኳስ አፍቃሪዎችም በቴሌቪዥን በማስተላለፍ በዚህ የጭንቀት ጊዜ የመዝናኛ አማራጭ እየፈጠረላቸው ነው።

ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ

'ኮሮናቫይረስን ትራክተር ያድነዋል'

የፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ 'ኮሮናቫይረስን ትራክተር ያድነዋል' ንግግር ብዙ ሰዎችን ያወዛገበ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ በማሕበራዊ ሚዲያ እያሽሟጠጡት ይገኛል።

ፕሬዝዳንቱ ማለት የፈለጉት 'እርሻ ቦታ ላይ ጠንከረን እንስራ' ነው።

ምንም እንኳ እራሳቸው ፕሬዝዳንቱ አልኮል የማይጠጡ ቢሆኑም ለዜጎቻቸው ግን ከቻላችሁ የተወሰነ ቮድካ ብትጎነጩበት የኮሮናቫይረስን ስርጭት መግታት ትችላላችሁ በማለትም መክረዋል።

ነገር ግን ከቤላሩስ ውጭ ባሉ የዓለም አገራት ላይ ቫይረሱ እያስከተለ ያለውን ቀውስ ስለሚያዩ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የአገሬው ሰዎች ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል።

በሚኒስክ ተማሪዎች ሰው ከተሰበሰበበት ቦታ ላለመገኘት ሲሉ ሆን ብለው ታምሜያለሁ በማለት እቤታቸው እየቀሩ ይገኛሉ።

ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተወሰኑ ሰዓታትን ብቻ ማስተማር ጀምረዋል።

በሚኒስክ በጣም ውስን ሰዎች ብቻ ወደ ጎዳና ይወጣሉ። በእድሜ የገፉ ሰዎችም የወረርሽኙ ቀዳሚ ተጠቂ መሆናቸው ግንዛቤው አለ። የሚገርመው ግን ይህ አይነቱ የግንዛቤ ፈጠራ ከባለስልጣናት ዘንድ የሚመጣው በጣም ውስኑ ነው።

ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ ሁሉም በዓለም አቀፍ በረራዎች በኩል ወደ ቤላሩስ የሚመጡ ሰዎች ስለሚመረመሩ ምንም መጨነቅ አያስፈልግም ብለዋል።

"በየቀኑ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ፖዚቲቭ ሆነው ይገኛሉ፤ ነገር ግን በለይቶ ማቆያ ውስጥ ለአንድ ወይም ሁለት ሳምንት ይቆዩና ይለቃቃሉ" በማለት ፕሬዝዳንቱ ለቫይረሱ መጨነቅ እንደማያስፈልግ በመግለጽ ዜጎቻቸውን አበረታትተዋል።

ባለፈው ሳምንት የተደረገ የእግር ኳስ ግጥሚያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ሳምንት የተደረገ የእግር ኳስ ግጥሚያ

'በፍርሃት የሚያሸብሩትን ፈልጓቸው'

ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ በፍርሃት መራድ ከቫይረሱ በላይ አደገኛ ነው ይላሉ። በዚህም ምክንያት ለአገሪቱን የደኅንነት መስሪያ ቤት [የቤላሩስ ኬጂቢ] እነዚህን "በፍርሃት የሚያሸብሩትን ፈልጓቸው" የሚል ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳ በይፋ ባይነገርም በቫይረሱ ሳይሆን እንዳልቀረ የተነገረላቸው ሁለት ሰዎች ሞተዋል።

የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት አካል የነበረችው ቤላሩስ በብዙ ነገር የተለየች አገር ነች። በአውሮፓ የሞት ቅጣትን ተግባራዊ የምታደርግ ብቸኛዋ አገር ነች። ባለስልጣናቷ በኮሮናቫይረስ ላይ ዘና ያለ አተያይ በመያዝም ከአውሮፓ በእጅጉ የተለዩ ናቸው።

ባልተለመደ መልኩ ለወትሮው ሁሉንም ነገር ካልተቃወምኩ ሲል የነበረው የቤላሩስ የተቃዋሚ አክቲቪስት አንድሬይ ኪም "ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ ልክ ናቸው። ምክንያቱም ቤላሩስ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴዋ ቢዘጋ ምጣኔ ሃብቷ ይሞታል" በማለት ከፕሬዝዳንቱ ጋር መስማማቱን ገልጿል።

"አሁን ነገሮች ላይ፣ ታች እየተዘበራረቁ ነው። በዚህ ወቅት ደግሞ መሪዎቿ በሕዝበኝነት የማይነዱ ነገር ግን ለዜጎቻቸው በጎ ነገር የሚመኙባት ብቸኛዋ የዓለም አገር ቤላሩስ ነች" በማለት አክሏል።

"ይህን በማለቴ ክፉኛ እንደምብጠለጠል አውቃለሁ፤ ነገር ግን በዚህ እብደት በነገሰበት ሁኔታ ውስጥ ዝም ብዬ መቀጠል አልፈልግም" በማለት ቀሪው ዓለም ስለኮሮናቫይረስ የሚያወራው "እብደት" መሆኑን ኪም አመላክቷል።

እርሱ እንደሚለው ቤላሩስ ከቫይረሱ ነጻ የምትሆነው የመመሪያ ጋጋታ በማውጣት ወይም ሌላ ነገረ በማድረግ ሳይሆን 'ምንም ባለማድረግ' ነው።

ኮሮና