ቅጥረኛው መፈንቅለ መንግሥት አሳላጭ በመቶ አመቱ ሞተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአለማችን ውስጥ መፈንቅለ መንግሥትን በማሳላጥ ዝናን ያተረፈው ማይክል በቅፅል ስሙ 'ማድ ማይክ' (እብዱ ማይክ) በመቶ አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
የዘር መሰረቱ ከአየርላንድ የሚመዘዘው 'ማድ ማይክ' የተወለደው በህንድ ነው።
ዝናውም ሆነ ስሙ መናኘት የጀመረው በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ1960ዎቹ ኮንጎ ላይ ባካሄደው ዘመቻ ነው።
መጨረሻዬን አሳምርልኝ ይሉ አዛውንት ከአመታት በኋላ አወዛጋቢ እንዲሁም መሳቂያ ሊሆን በቅቷል።
በተለይም በጎርጎሳውያኑ በ1981 ሲቨልስ ላይ ባካሄደው የከሸፈ መፈንቅለ መንግሥት ሙያዬ ብሎ የሚጠራው አሳላጭነት ባሳፋሪ ሁኔታ ተቋጨ።
የሁዋሬ ልጅ ክሪስ በደቡብ አፍሪካዋ ከተማ ደርባን በሚገኝ የጤና ተቋም ህይወቱ ማለፉን ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
"ማይክ ሁዋሬ የህይወትን ጣፋጭነት የምታውቀው በአደገኛ ሁኔታ ስትኖር ነው የሚል የህይወት ፍልስፍና ነበረው። ይህንን ያህል እድሜ መኖሩም የሚገርም ነው" በማለት መግለጫው ያትታል ።
ከአካውንትነት ወደ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለእንግሊዝ ጦር ተሰልፎ ተዋግቷል። ከጦርነቱ በኋላ በአካውንትነት ሙያው ቀጠለ፤ በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ ጥቃቅን ንግዶችንም ጎን ለጎን ያካሂድ ነበር።
ይህንን የሚቀይር ሁኔታ የተከሰተው በጎርጎሳውያኑ 1961 ሲሆን ሞይሴ ትሾምፔ የተባለ የኮንጎ ፖለቲከኛና ነጋዴ ጋር በተፈጠረለት የትውውቅ እድል ነው።
ከተዋወቁ ከሶስት አመታት በኋላ ሞይሴ ትሾምፔ የኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም በኮሚዩኒስቶች ድጋፍ የነበረውን የኮንጎ አማፂ ቡድን ፍርስርሱን እንዲያወጣ ማይክን ቀጠረው።
ማይክም ሌሎች ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮችን ሰብስቦ አስራ ስምንት ወራት በፈጀ ዘመቻ አማፂ ቡድኑን አከርካሪውን መስበር ችሏል።
ፀረ- ኮሚዩኒስት እምነቱም ኮሚዩኒዝምን በማይደግፉ አገራት ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ሊያተርፍ ችሏል።
በወቅቱም የምስራቅ ጀርመን ሬድዮ "እብዱ አዳኝ ውሻ" በሚልም ይጠራው ጀመር፤ በዚህም እብዱ ማይክ የሚለው ቅፅል ስምም በጣም አስደስቶት ነበር ተብሏል።
በጎርጎሳውያኑ 1978 በጀብደኝት የተሞላ "ዋይልድ ጂዝ" የሚል ፊልምም እንዲሰራ ምክንያት ሆኗል።
ሪቻርድ በርተን የተባለው ተዋናይም የእብዱ ማይክ ገፀ ባሕርይን ተላብሶ ተጫውቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምንም እንኳን በኮንጎ ያከናወነው ጀብድ አለም አቀፍ ክብር ቢያስገኝለትም ከዚያ በኋላ በሲሸልስ ያከናወነው መሳቂያ አድርጎታል።
"የመዝናኛው መፈንቅለ መንግሥት"
ከጦር ህይወቱ በጎርጎሳውያኑ 1980ዎቹ በጡረታ የተገለለው እብዱ ማይክ የሲሸልስን መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት ለመጣልም ያቀደው በጎርጎሳውያኑ 1981 ነበር።
የሲሸልስን ወጣ ገባ በደንብ ያውቀው ነበር የሚባለው ማይክ በወቅቱ ሃገሪቷን ይመሩ ለነበሩት ሶሻሊስቱ ፕሬዚዳንት አልበርት ሬኔ ከፍተኛ ጥላቻ ነበረው።
መፈንቅለ መንግሥቱን ለማካሄድ ከደቡብ አፍሪካና ኬንያ መንግሥታት ድጋፍ የነበረው እብዱ ማይክ ሴራውን ሃ ብሎ ጀመረ።
በጎርጎሳውያኑ ጥቅምት ወር 1981 የጦር መሳሪያውንም ከከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ቤቱ ከመሬት በታች ከሚገኘው የወይን ማስቀመጫ መጋዘኑ ጋር አከማቸ።
መፈንቅለ መንግሥቱንም ለማካሄድ አርባ ስድስት ወንዶችንም በመልመል ጉዞውንም ወደ ሲሸልስ አደረገ።
የቀድሞ የራግቢ ተጫዎቾችንም በማስመሰል ወደ ሲሸልስ ገቡ።
አብዛኛዎቹ ተመልማዮች የማሄ አለም አየር መንገድ ጉምሩክን ማለፍ ቢችሉም፤ አንደኛው ቅጥረኛ በስህተት ሌላ ሰልፍ ውስጥ ገብተው ከአንድ የጉምሩክ ባለስልጣን ጋር በተፈጠረ እሰጣገባ ሻንጣው እንዲፈተሽ ተወሰነ።
የአየር መንገዱ ፈታሾችም ኤኬ-47 ጠመንጃ አንደኛው ግለሰብ ላይ ባገኙትበትም ወቅት፣ ሰውየው ደንግጦ ውጭም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ እንዳላቸው አጋለጠ።
አጠቃላይ እቅዱ አጣብቂኝ ውስጥ የገባውና አየር መንገዱ እየተናጠ ባለበት ሰዓት ቅጥረኞቹ የህንድ አውሮፕላንን በቁጥጥር ስር በማዋል ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመለሱ።
ደቡብ አፍሪካም በደረሱበት ወቅት ቅጥረኞቹ ዘብጥያ ወረዱ፤ የእብዱ ማይክ የመፈንቅለ መንግሥትም በአለም አቀፍ ሚዲያ ዘንድ መዘባበቻ ሆነ።
ከአመትም በኋላም የህንድን አውሮፕላን በመጥለፍ ክስ ተመሰረተባቸው። እብዱ ማይክ ሃያ አመት ቢፈረድበትም ከሰላሳ ሶስት ወራት እስር በኋላ ነፃ ሆኗል።
የመጨረሻ እድሜውን በደቡብ አፍሪካ ያሳለፈው እብዱ ማይክ 'መርሰናሪ'፣ 'ሮድ ቱ ካላማታ' የሚሉ መፃህፍትን አሳትሟል።












