የሶሪያ ጦር ወሳኝ ያላትን ከተማ ከታጣቂ ኃይሎች ነጻ ማውጣቱን አስታወቀ

የሶሪያ ጦር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የበሽር አላሳድ ጦር በኢድሊብ ግዛት የምትገኘው ማራት አል-ኑማን የተሰኘች ስትራቴጂካዊ ከተማ ከታጣቂ ኃይሎች ነጻ ማውጣቱን አስታወቀ።

የሶሪያ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የአገሪቱ ጦር ከከፍተኛ ውጊያ በኋላ ከተማዋን መቆጣጠሩን አውጇል።

በመንግሥት እና በታጣቂ ኃይሎች መካከል በከተማዋ የተደረገውን ጦርነት ሽሽት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ቱርክ ድንበር ተጠግተዋል።

ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው የበሽር አላሳድ ጦር ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ ከፈንጂ እና ከሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች እያጸዳ መሆኑ ተነግሯል።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም የደረገው የሶሪያ ኦብዘርቫቶሪ ፎር ሂዩማን ራይትስ የተሰኘ ድርጅት እንዳለው ከሆነ፤ ከተማዋን ተቆጣጥረዋት የነበሩት ታጣቂ ኃይሎች ከሳለፍነው አርብ ጀምሮ ከተማዋን ጥለው መውጣት ጀምረው ነበር።

በሩሲያ አየር ኃይል የሚደገፉት የበሽር አላሳድ ወታደሮች ከተማዋን እና በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ 25 መንደሮችን መቆጣጠራቸውን ይሄው ድርጅት አስታውቋል።

ማራት አል-ኑማን የተኘችውን ስትራቴጂካዊ ከተማን ለመቆጣጠር በተደገው ጦርነት 147 የሶሪያ መንግሥት እና 151 የታጣቂ ኃይሎች ወታደሮች መገደላቸው ተነግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት በሶሪያ የሚደረጉት ጦርነቶች ለበርካታ ንጹሃን ዜጎች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት እንደሆኑ አስታውቋል። ባሳለፈው አንድ ወር ብቻ በሁለቱ ኃይሎች መካከል እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ጠንካራ ጦርነት አስክ 358 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።

ወቅቱ በሶሪያ ከፍተኛ ቅዝቃዜ የሚመዘገብበት መሆኑ የተፈናቃዮቹን ህይወት አደጋ ላይ እንደሚጥል የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።