ለ12 ቀናት በሰዋራ ሥፍራ የቆዩት አውስትራሊያዊት በሕይወት ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, NT Police
በአውስትራሊያ ገጠራማ ቦታ አንድት ሴት ከከተማ ውጭ ባለ ጥሻ አቅራቢያ ከ12 ቀናት በኋላ በሕይወት መገኘታቸው ተዘገበ። ግለሰቧ ብስኩት እና ከውሃ ጉድጓድ ውሃ እየተጎነጩ እንደቆዩ ታውቋል።
ታምራ ማክቢዝ የተሰኙት እኝህ አውስትራሊያዊት እና ሌሎች ሁለት ሰዎች ሲጓዙበት የነበረው መኪና በአንድ ወንዝ ውስጥ በመግባቱ መውጣት ተስኗቸው ቆይተዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች እርዳታ ለማግኘት ሲሉ ተከፋፍለው በየፊናቸው ተሰማሩ። በዚያው አቅራቢያ ለመቆየት የወሰኑት ታምራ ማክቢዝ ሪሊይ ግን ከመኪናቸው አቅራቢያ ሲገኙ ሌሎቹ ሰዎች አሁንም የደረሱበት አልታወቀም።
የ52 ዓመቷ ሴት፣ ክሌር ሆክሪግ እና ፕሁ ትራን ጋር በመሆን ከአገሪቷ ሰሜናዊ ግዛት አልሴ ስፕሪንግስ ከተሰኘ ከተማ አቅራቢያ እያሽከረከሩ ሳለ ነበር ከአንድ ትልቅ ወንዝ ዳርቻ የተደነቀሩት።
የታምራ ማክቢዝ ውሻም አብራቸው ነበረች።
ማክቢዝ ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ለመውጣት ሲታገሉ ለሦስት ቀናት ያህል በመኪናው አቅራቢያ ቆይተዋል።
"ለመውጣት ብዙ ጊዜ ሞክረናል፤ ነገር ግን ወንዙ ትልቅ በመሆኑ ልንወጣ አልቻልንም" ይላሉ እኝሁ ነፍሳቸው የተረፈላቸው ሴት።
በዚያ ቀን አየሩ በጣም ይሞቅ ስለነበር መኪና ውስጥ ገባን ፤ ምሽቱንም መኪናው ውስጥ መተኛት ቻልን" የሚሉት ማክቢዝ በመኪና ውስጥ የያዙትን ምግብና መጠጥ ረሃባቸውን እንዳስታገሰላቸው ይናገራሉ።
ከዚያ በኋላ ግን እርዳታ ለማግኘት ሲሉ ተከፋፈሉ። ትራንና ሆክሪጅ ወደ መንገዱ ለመሄድ አቀዱ። ማክቢዝ ግን ውሻቸው አብራቸው በመሆኗ እዚያው አቅራቢያ ለመቆየት ወሰኑ።
ታዲያ ይህንኑ የተመለከተ አንድ የአካባቢው ነዋሪ አንድ ተሽከርካሪ ማየቱን በመጠቆሙ የአገሪቷ ሰሜናዊ ግዛት ፖሊስ ሄሊኮፕተር አሰማርቶ መፈለግ ጀመረ። ማክቢዝ ከመኪናቸው 1.5 ኪሎሜትር በሚርቅ ሥፍራ ታዩ። ወደ ሆስፒታል ተወስደው እያገገሙ ይገኛሉ። በአቅራቢያቸው ያለውን የጉድጓድ ውሃ እየጠጡ መሰንበታቸውም ነፍሳቸውን አቆይቶላቸዋል።
ውሻቸው ግን ይገኝ አይገኝ የታወቀ ነገር የለም።
ፖሊስ ቀሪዎቹን ግለሰቦችም መፈለጉን ቀጥሏል።













