ኳታር የኤርትራን ክስ 'ሐሰተኛ' ስትል ውድቅ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኳታር ከፍተኛ ባለስልጣኖቼን ለመግደል ዕቅድ አላት በማለት ኤርትራ ያቀረበቸውን ክስ የኳታር መንግሥት አጣጣለው።
በኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር በኩል ለወጣው ክስ አዘል መግለጫ ኳታር በሰጠችው ምላሽ "ሐሰት" በማለት ክሱን ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርጋዋለች።
የኤርትራ መንግሥት በተጨማሪም ኳታር ተቃዋሚ ቡድኖችን በመደገፍ በኤርትራ መንግሥት ላይ አመጽና ተቃውሞን ለመቀስቀስ መጣሯን በክሱ ላይ አመልክቷል።
ኳታር ባወጣችው መግለጫ የኤርትራ መንግሥት ከጠቀሳቸው የትኛውም አንጃ ሆነ ቡድን ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላት በመግለጽ "ይህንንም የኤርትራ መንግሥት በደንብ ያውቀዋል" ብላለች።
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የሚታወቁትን ሌሎች ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ መንገዶችን ከመጠቀም ይልቅ" በኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በወጣው መግለጫ ግራ መጋባቱን ጠቅሷል።
የኳታር የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ ከዚህ ቀደም ከኤርትራ ጋር መልካም ግንኙነት እንደነበረውና ለዚህም የተለያዩ ተግባራት ሲያከናወኑ መቆየታቸውን፤ ኤርትራ ከጂቡቲ ጋር ያላትን ያለመግባባት ለመፍታት ኳታር ያደረገቸውን ጥረት በምሳሌነት አንስቷል።
የኤርትራ መንግሥት በመግለጫው ላይ ኳታር "የኤርትራ መንግሥት በእስላማዊ ተቃዋሚዎች መካከል ጽንፈኛ ሐይማኖታዊ አመለካከቶችን በማስረጽ አመጽ በመቀስቀስ፣ በወገኖቻቸው ላይ እንዲነሱ" ፍላጎት አላት ሲል ይከሳል።
በቅርቡ የወደብ ከተማዋን ፖርት ሱዳንን ጨምሮ በምሥራቃዊ ሱዳን፣ በነዋሪዎች መካከል ተከስተው የነበሩ ግጭቶችን በማንሳት ኤርትራ በመግለጫዋ ኳታርን "ፖርት ሱዳን ውስጥ የጎሳ ግጭቶች እንዲከሰቱ" በማድረግ ወቀሳ ሰንዝራለች።
የኤርትራን ክስ ተከትሎም የኳታር የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ የኤርትራ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር "ከክስና ሐሰተኛ መረጃዎችን ከመጠቀም ይልቅ እውነታዎችንና የችግሮቹን ስር መሰረት መለስ ብሎ እንዲመረምር" ጥሪ አቅርቧል።
በባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል ያጋጠመው ቀውስ እስከተፈጠረበት ጊዜ ድረስ ኤርትራ ከኳታር ጋር ለረዥም ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት ነበራት።
በሳዑዲ አረቢያ በሚመሩት አገራትና በኳታር መካከል አለመግባባቱ ሲፈጠር ኤርትራ ወዳጅነቷን ከሳዑዲና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጎን በመቆም የመን ውስጥ የሚካሄደውን ዘመቻ ደግፋለች።
በዚህም ሳቢያ አገራቱ የመን ውስጥ የሚያካሂዱትን ዘመቻ ለማገዝ ኤርትራ ከወደብ ከተማዋ አሰብ ወጣ ብሎ የሚገኝ ወታደረዊ ሰፈርን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሠራዊት እንዲጠቀምበት ፈቅዳለች።















