የኤርትራ መንግሥት፡ ኳታር ባለስልጣኖቼን ለመግደል ዕቅድ አላት

የፎቶው ባለመብት, IOM
ኳታር የተለያዩ ኃይሎችን በመጠቀም የአገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት ለመግደል ዕቅድ እንዳላት እንደደረሰበት የኤርትራ መንግሥት ይፋ አደረገ።
የኤርትራ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው ኳታር የተለያዩ የሽብርና የተቃውሞ ተግባራት በኤርትራ ውስጥ እንዲፈጸሙ የማስተባበር ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን እንደደረሰበትም አስታወቀ።
ለዚህም ተግባር ጎረቤት ሱዳንን እንደ ድልድይ በመጠቀም የአገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ የተለያዩ ተግባራት በኳታር ደጋፊነት እየተከናወኑ መሆናቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
'ኳታርና ተላላኪዎቿ' እብደታቸው እያደገ ነው ብሎ የሚጀምረው መግለጫው "ኳታርና ሸሪኮቿ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎችና የፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም ወጣቶችን በመቀስቀስ የጦር መሳሪያ እንዲታጠቁና ተቃውሞ እንዲያስነሱ ተዘጋጅታለች" ሲል ይከሳል።
መግለጫው "ሙስሊም የኤርትራ ተቃዋሚዎችን ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶችን በመስበክ በኤርትራ ሕዝብ መካከል የብሔር ጥላቻ በመዝራት፣ ሙስሊሞች በሌላው ሕዝብ ላይ እንዲነሱ የሐሰት ወሬ እያሰራጨች ነው" ይላል።
በተጨማሪም በኤርትራ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳሉ የሚያሳዩ ቪድዮዎችን በማዘጋጀት ተቃውሞና አድማዎች እንዲካሄዱ በማበረታታትና የጦር መሳሪያዎችን በማቅረብ የኤርትራ መንግሥት ኳታርን ይከሳል።
በዚህም የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ተቋሞች ላይ ጥቃት እንዲፈጸምና ውድመት እንዲደርስ እንዲሁም አስፈላጊ እና ተጽእኖ ፈጣሪ የመንግሥት ባለስልጣናትን ለመግደል ስልጠና እየሰጠች ነው ይላል።
በምሥራቃዊ ሱዳን በብሔሮች መካከል ግጭት መፍጠርን በሚመለከትም 'አጃኢብ የሚያሰኝ ዕቅድ' ተዘጋጅቶ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን መግለጫው ያመለክታል።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ የኤርትራ መንግሥት ቱርክ እና ኳታር በኤርትራ ላይ አውዳሚ ተግባራት ለመፈጸም እየተዘጋጁ እንደሆነ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ገልጾ ነበር።
ቱርክ በዚህ ዓመት 'የኤርትራ ዑላማ ምክር ቤት' በሚል የሚታወቀው ቡድን ጽህፈት ቤቱን እንዲከፍት መፍቀድዋን ጠቅሶ ይህም መግለጫው 'አውዳሚ' ላለው አላማ እንደሚውል ይገልጻል።
የኤርትራ ዑላማ ምክር ቤት (መጅልስ ሹራ ራቢጣ ዑላማእ ኤሪትሪያ) በሱዳን ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደሌለው የቡድኑ አባል የሆኑት መሓመድ ጁማ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የኤርትራ መንግሥት "ይህንን ከንቱ ተግባር በተለያየ መንገድ በመደገፍ በኩል ኳታርና ለእንደዚህ እኩይ አላማ ግዛቱን አሳልፎ በሰጠው የሱዳን ሥርዓት አማካይነት የሚፈጸሙ ናቸው" ሲል ከሶ ነበር።
ኤርትራ ከኳታር ጋር የነበራት ጠንካራ ዝምድና በመሻከሩ በሳዑዲ አረቢያ ወደ ሚመራውን የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ጥምረት ፊቷን አዙራለች።
ከአራት ዓመታት በፊት በየመን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለፈጸመው በሳዑዲ የሚመራውን ኅብረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ኤርታራ አስታውቃ ነበር።
ሳዑዲና አረብ ኤምሬቶች የሚገኙበት የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጥምረት ኳታርን ካገለሉና የየብስና የባሕር መተላላፊያ ማእቀቦችን ከጣሉባት በኋላ ቱርክ የኳታር ሸሪክ መሆንዋን ይታወሳል።















