በጥይት ተመትተው የነበሩት ጄነራል ስብሐት ኤፍሬም ወደ ኤርትራ ተመለሱ

የፎቶው ባለመብት, ERi-TV
ባለፈው ታኅሳስ ወር ላይ ማንነቱ ባልተገለጸ ግለሰብ በጥይት ተመትተው ውጪ ሃገር በህክምና ላይ የቆዩት የኤርትራው ኃይልና ማዕድን ሚኒስትር ጄነራል ስብሐት ኤፍሬም ወደ ሃገራቸው እንደተመለሱ ተገለጸ።
ጉዳዩን በተመለከተ ከመጀመሪያው አንስቶ በጄኔራሉ ላይ ስለደረሰው ጥቃት በትዊተር ገጻቸው ላይ መረጃ ሲሰጡ የነበሩት በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር አቶ እስጢፋኖስ አፈወርቅ እንዳሰፈሩት ጄነራል ስብሐት ኤፍሬም ህክምናቸውን አጠናቀው ተመልሰዋል።
አምባሳደር እስጢፋኖስ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት "ጄነራል ስብሐት ኤፍሬም በውጪ ሃገር ሲከታተሉ የነበረውን ህክምና በተሳካ ሁኔታ አጠናቀው ከሚወዱት ቤተሰባቸው ጋር ወደ አሥመራ መመለሳቸውን በመስማቴ ደስተኛ ነኝ" ብለዋል።
የኤርትራ መንግሥት በጄነራሉ ላይ ስለተፈጸመው ጥቃትም ሆነ አሁን ህክምናቸውን ጨርሰው ስለመመለሳቸው በይፋ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ጄነራል ስብሐት ኤፍሬም ላይ ደረሰ የተባለው ጥቃት በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ አድብቶ በነበረ አንድ ግለሰብ መፈፀሙንና ግለሰቡም በቁጥጥር ስር እንደዋለ በወቅቱ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ከአሥመራ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ጄነራሉ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው በኋላ የተባበሩት አረብ ኤምሬት ውስጥ የሚገኝ ነገር ግን ስሙ ያልተጠቀሰ ሆስፒታል ውስጥ ከፍተኛ ህክምና እንዲያገኙ መወሰዳቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
ጄኔራል ስብሐት የኃይልና ማዕድን ሚኒስትር ከመሆናቸው ቀደም ብሎ ለ19 ዓመታት የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ሲሆን፤ ከዚያ በፊት ደግሞ የአሥመራ ከተማ አስተዳደርና የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ነበሩ።
ጄኔራል ስብሐት ኤፍሬም ከሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ ከፍተኛ አመራሮች አንዱ ሲሆኑ የፖለቲካ ጽህፈት ቤት አባልም ናቸው።












