እየከበዱ የመጡት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ችግሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአዲስ አበባ ያለውን የሕዝብ ትራስፖርት ችግር ለመቅረፍ በሁለት ዋነኛ መስመሮች ከአራት ዓመት በፊት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ቀላል ባቡር ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች እየተዳከመ መሆኑን ተገልጋዮችና የድርጅቱ ሰራተኞች ይናገራሉ።
አብዱልማሊክ አሊ በአብዛኛው የባቡር አገልግሎት ይጠቀማል። "ባቡሩ እንደታሰበው ቶሎ ቶሎ አይመጣም፤ አንዳንዴም ብልሽት አጋጥሞት መንገድ ላይ ይቆማል" ይላል። ይሄው ችግር አጋጥሞት በእግሩ የተጓዘበትን አጋጣሚ ያስታውሳል። ተገልጋዮች በዝናብና በፀሐይ ሳይንገላቱና ሳይጉላሉ አገልግሎቱን መጠቀም ቢችሉ ምኞቱ ነው።
ብዙ ጊዜ ከአውቶብስ ተራ - ሳሪስና ከአውቶብስ ተራ - ስታዲም ለመሄድ እገለገልበታለሁ ያሉን ሌላኛው የባቡር አገልግሎት ተጠቃሚ አቶ ዘለቀ ናቸው፤ ልክ አንደ አብዱልማሊክ ሁሉ እርሳቸውም የባቡሩ መዘግየት ያማርራቸዋል።
ባነጋገርናቸው ጊዜም ባቡሩን ሲጠብቁ 45 ደቂቃ ገደማ እንዳሳለፉ ነግረውናል። ከዚህ ቀደምም በኃይል መቋረጥ ምክንያት ጉዟቸው ተስተጓጉሎ እንደነበር አይዘነጉትም፤ የባቡሮቹ ቁጥርና የተሳፋሪዎች ብዛት አለመመጣጠኑም ችግር እንደሆነባቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው የባቡር አገልግሎቱ ሲጀምር አንስቶ በባቡር አሽከርካሪነት (ትሬይን ማስተር) ሲሰራ የቆው የድርጅቱ ባልደረባ እንደሚለው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በአገልግሎት ላይ የሚገኙት ባቡሮች፤ ድርጅቱ ካሉት መካከል ግማሽ ያህሎቹ ብቻ ናቸው።
በተለይ ለባቡሮቹ የሚያስፈልገው መለዋወጫ በቀላሉ ስለማይገኝ ትናንሽ እክሎች ሳይቀሩ ባቡሮቹን ለመቆም ያስገድዷቸዋል።
የድርጅቱ የጥገና ሰራተኞች እንደሚናገሩት መለዋወጫዎች ከቻይና ስለሚመጡ ሂደቱ አዝጋሚና ጊዜን የሚፈጅ በመሆኑ ባቡሮቹ ለወራት ከአገልግሎት ውጪ ይሆናሉ።
የቀላል ባቡሮቹን የሚጠቀመው ሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም የአገልግሎታቸው አቅም ግን እየቀነሰ መሆኑን የሚናገሩት ሰራተኞቹ ባቡሮቹ በሚገጥሟቸው ችግሮች የተነሳ በጥንድ ፉርጎዎች የሚሰጠው አገልግሎት ቁጥር በተለያዩ ጊዜያት እየቀነሰ በአንድ ፉርጎ ብቻ ውስን ሰዎችን ሲያጓጉዙ በተደጋጋሚ ይታያል።
በተጨማሪም ድርጅቱ ለሰራተኞቹ ከሚሰጠው ክፍያና ጥቅማጥቅም አንጻር ባለፈው ዓመት ሰራተኞቹ ባካሄዱት የሥራ ማቆም አድማ ምክንያት አገልግሎቱ ተስተጓጉሎ ነበር። ያናገርናቸው የባቡር አሽከርካሪዎች እንደሚሉት ባነሷቸው የተወሰኑ ጥያቄዎች ላይ ማሻሻያ መኖሩን ቢናገሩም ባለው ሁኔታ ግን ደስተኛ አይደሉም።
"የምንለብሰው የደንብ ልብስ እንኳን ባቡሩ ሥራ ሲጀምር የተሰጡን ናቸው፤ አንዳንዶቻችን የደንብ ልብሳችን በማለቁ በእራሳችን ልብስ ነው ሥራችንን የምናከናውነው" ሲል የሚናገረው ሌላኛው የባቡር አሽከርካሪ፤ "ድርጅቱ ከበድ ያሉ ችግሮቹን በአጭር ጊዜ ይፈታል ብሎ ለማሰብ እቸገራለሁ" ይላል።
ባቡሮቹ በአገልግሎት ሂደት እያረጁ ስለሚሄዱ ተገቢው ጥገናና ለውጥ ቢያስፈልጋቸውም ያንን የማድረጉ ነገር ቀላል እንዳልሆነ አሽከርካሪዎችና የጥገና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው አሽከርካሪ እንደሚለው አንዳንድ ወሳኝ የባቡሩ ክፍሎች በየጊዜው ካልተለወጡ ችግር ስሚያስከትሉ ስጋት አለብን ይላል። "የአንዳንድ ባቡሮች ፍሬን በጊዜ ሂደት እየተዳከሙ በመሄዱ በጉዞ ላይ እያሉ በድንገት ሰው ወይም መኪና በመንገዳቸው ገብቶ ለማቆም ቢገደዱ ያንን ማድረግ ስለሚቸገሩ አደጋ ሊከሰት ይችላል" ይላል።
በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ መቋረጥ በርካታ ተሳፋሪዎችን እያማረረ ያለ ሆኗል። በድንገት የሚከሰተው የኤሌክትሪክ መቋረጥ ተሳፋሪዎችን ግማሽ መንገድ ላይ እንዲወርዱ አሊያም ለሰዓታት በባቡሩ ውስጥ እንዲቀመጡ ያስገድዳል።
"ተሳፋሪው እኛ ያለንበትን ሁኔታ ስለማይረዳ ቁጣውንና ንዴቱን እኛ ላይ ያሳርፋል፤ ይህ ደግሞ ለእኛ ሁለት ቅጣት ነው" ሲል ምሬቱን ይናገራል።
በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ጥቂት የከተማ ውስጥ ቀላል የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቶች ውስጥ የሚጠቀሰው የአዲስ አበባው ባቡር በአራት ዓመት ውስጥ ባሳላፈው ጉዞ ፈተናዎች ገጥመውታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ካለበት መሰረታዊ ችግሮች በስተቀር ባቡሮቹ አሁንም አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት የኃይል መቆራረጥና የመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት ፈተና ቢሆንም ካሉት 41 ባቡሮች 34 የሚሆኑት አሁንም ለአገልግሎት ዝግጁ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 2 ባቡሮች እንደመጠባበቂያ ይቀመጣሉ። በመሆኑም ከ20-28 ባቡሮች በየቀኑ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ናቸው።
ባሉት ችግሮች ሳቢያ ሁሉንም ባቡሮች በሙሉ አቅም ማሰራት እንዳልተቻለ ግን አልሸሸጉም።
ይህም ችግር ባቡሮቹ ቀድሞ በተያዘላቸው እቅድ በየ6 ደቂቃው በእያንዳንዱ የባቡር ጣቢያ ይደርሳሉ መባሉን አፍርሶታል፤ በ40 ደቂቃ ግፋ ሲልም ለአንድ ሰዓት መዘግየታቸውን የተለመደ አድርጎት ነበር። አሁን ግን ተሻሽሎ ለ15 ደቂቃ ዝቅ ማለቱን ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ከቻይና መንግስት ጋር ያላቸው ውል መለዋወጫን ስለማያካትት ለመንግስት ተጨማሪ የመለዋወጫ በጀት ለማቅረብ መገደዳቸውን ይናገራሉ።
ለዚህም ባቡሩ አገልግሎት እየሰጠ መለዋወጫዎቹን ማቅረብ ይቻላል በሚል እሳቤ በስምምነቱ ሳይካተት መቅረቱን ያስታውሳሉ፤ አገሪቷ እየገጠማት ባለው የውጭ ምንዛሬ እጥረትም ይህንን ሙሉ በሙሉ ማሟላት አልተቻለም ይላሉ።
ጥገናውን አስመልክቶም ለሁለት የቻይና ኩባንያዎች የ3 ዓመት ኮንትራት የተሰጠ ሲሆን የጥገና ስራ፣ የሰው ኃይል የማሰልጠንና ባቡሩን የማስተዳደር ሥራ ይሰራሉ። ነገርግን ቀስበቀስ ኃላፊነቱን ኢትዮጵያውያን እየተረከቡ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
"ስምምነቱ ለአንድ ዓመት ባይራዘም ኖሮ፤ እስካሁን ኢትዮጵያውያን ሥራውን ሙሉ ለሙሉ ይረከቡ ነበር" ብለዋል።
አሁን ላይ ያለውን ችግር ለማቃለልም ቢያንስ 15 ኪሎ ሜትር የሚሆን የኤሌክትሪክ ገመዶችን የተቀየረ ሲሆን የባቡሮቹን ሙሉ አቅም ለመጠቀም እየተሰራ ነው። መለዋወጫዎቹ ተገዝተው ጥገና ሲደረግላቸው አገልግሎቱ እንደሚሻሻል ተስፋ ሰጥተዋል።
እስከ አሁን የትኛውም አካባቢ ላይ በእቅድ ደረጃ የተያዘ ሌላ የባቡር ማስፋፊያና አዲስ ፕሮጀክት አለመኖሩንና የባቡሮቹን ቁጥር የማሳደጉም ጉዳይ አገሪቷ ባላት የገንዘብ አቅም እንደሚወሰን አክለዋል።















