የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የሌሎች ሃገራት ስደተኞች ሊቢያ ወደብ ላይ ከመርከብ አንወርድም እያሉ ነው

የፎቶው ባለመብት, MSF Sea
ሊቢያ ወደብ የደረሱ ስደተኞች ህይወታቸውን ካተረፈቻቸው የዕቃ ጫኝ መርከብ አንወርድም እያሉ ነው።
ቀደም ሲል በአዘዋዋሪዎች ግፍ እንደደረሰባቸው የሚናገሩት ስደተኞቹ በአስገዳጅ ሁኔታ ከመርከቧ ከመውረድ መሞትን እንደሚመርጡ ተናግረዋል።
ስደተኞቹ ከሳምንት በፊት ነበር ከሊቢያ ምዕራባዊ ወደብ ወደ ሚዝራታ ያቀኑት።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫን ጠቅሶ ኤ ኤፍ ፒ እንደዘገበው ስደተኞቹ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የፓኪስታን፣ የባንግላዴሽ እና የሶማሊያ ዜጎች ናቸው።
ባለፈው ረቡዕ ህጻናትንና እና ልጅ የያዘች እናትን ጨምሮ 14 ሰዎች ከመርከቧ በመውጣት ወደ ሊቢያ የስደተኞች ማቆያ መግባታቸውን አልጀዚራ ጠቅሶ 77 ሰዎች እስከትላንት ድረስ ከመርከቧ ለመውጣት ፈቃዳኛ አለመሆናቸውን ዘግቧል።
የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞች የህክምና ድጋፍ እየሰጧቸው ሲሆን መርከቧ ውስጥ የቀሩት "ተስፋ የመቁረጥ ምልክት እየታየባቸው ነው" ብለዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ

ስደተኞች የፓናማን ሠንደቅ ዓላማ በምታውለብልበውና ኒቪን በምትባለው መርከብ ላይ የተሳፈሩት ጥቅምት 29 ነበር።
"እንዴት ከመርከቡ ውረዱና ሊቢያ ቆዩ ትሉናላችሁ?" ሲል የሚጠይቀው የ17 ዓመቱ ሱዳናዊ ቢክቶር ከሬውተርስ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ "ከሊቢያ ውጭ ወደየትኛውም ቦታ ለመሄድ ዝግጁ ነን" ብሏል።
እንደ ቢክቶር ከሆነ በደቡባዊ ትሪፖሊ በሚገኘው ባኒ ዋሊድ የስደተኞች ማቆያ ወንድሙ እና ጓደኛው በአዘዋዋሪዎች እጅ ህይወታቸው አልፏል።
ሌሎቹ ስደተኞች የመርከብ ጉዞውን የጀመሩት ወደ ማልታ ለመሄድ በማሰብ እንደሆነ ለአልጀዚራ ገልጸዋል።
"ሁሉም ሰው የሚለው እዚሁ እንሞታለን እንጂ ከመርከቧ አንወርድም ነው" ሲል የደቡብ ሱዳን ዜግነት ያለው የ18 ዓመቱ ካኢ አስታውቋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስደተኞቹ ያለፍላጎታቸው ከመርከቧ እንዲወርዱ ተደርጎ "የተለያዩ እንግልቶችን ወደሚያስተናግዱባቸው የሊቢያ የስደተኞች ማቆያዎች" ሊገቡ አይገባም ብሏል።
ሊቢያ በህገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ የሚያቀኑ ስደተኞች መተላለፊያ ማዕከል ናት።












