የአውሮፓ ኀብረት በስደተኞች ጉዳይ ከስምምነት ደረሰ

አፍሪካዊ ስደተኛ በአውሮፓ

የፎቶው ባለመብት, SOPA Images

የአውሮፓ ኅብረት ከእልህ አስጨራሽ ድርድርና ውይይት በኋላ በስደተኞች ጉዳይ ከስምምነት ደርሷል።

በቤልጅየም ብራስልስ የተሰበሰቡት የአውሮፓ መሪዎች 10 ሰዓታት የፈጀ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው ስምምነት ላይ የደረሱት።

ጣሊያን ወደ አገሯ ባሕር አቋርጠው የሚገቡ ስደተኞችን በመቀበል ረገድ ሌሎች የኀብረቱ አባላት የማያግዟት ከሆነ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውሳኔውን እንደምትቀለብስ ማስፈራሪያ ስታቀርብ ነበር።

አሁን አዲሱ ስምምነት የስደተኛ መቀበያ ማዕከላት በሁሉም የኅብረቱ አገራት እንዲቋቋም የሚያበረታታ ነው። አገራቱ ማዕከላቱን ለማቋቋም አስገዳጅ ግዴታ ውስጥ ባይገቡም በፍቃደኝነት ላይ ተመሥርተው ግን ይህንኑ እንዲያደርጉ ስምምነቱ ያበረታታል።

እነዚህ ወደፊት የሚቋቋሙት የስደተኛ ማዕከላት ማን ወደ አገሩ መመለስ እንዳለበትና የትኛው ስደተኛ ከለላ ማግኘት እንዳለበት ይወስናሉ፤ የማጣራት ሥራውንም ያሳልጣሉ ተብሏል።

የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዚዳንት አገራቱ በመጨረሻ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከስምምነት መድረሳቸውን ያሳወቁት ከሰዓታት በፊት በትዊተር ገጻቸው ነው።

ማልታ- አውሮፓ ስደተኞችን የጫነች መርከብ

የፎቶው ባለመብት, MATTHEW MIRABELLI

የ28 አገራት የኅብረቱ መሪዎች የስደተኛ ማዕከላትን ከማቋቁም ስምምነት ባሻገር ቱርክ፣ ሞሮኮና ሌሎች የሰሜን አፍሪካ አገራት ድንበሮቻቸውን እንዲቆጣጠሩ የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የኅብረቱ አገራት ከስምምነት ደርሰዋል።

ጣሊያንና ግሪክ ሌሎች አገሮች የስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ እገዛ እስካላደረጉ ድረስ ምንም ዓይነት ስምምነት ላለመፈረም ሲዝቱ ነበር።

የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርከል ከስብሰባው ቀደም ብሎ የስደተኞች ጉዳይ የኅብረቱን ሕልውና የሚወስን ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው ነበር። የፖለቲካ ተንታኞች አውሮፓ ኅብረት የስደተኞች ጉዳይ ቀውስ ውስጥ ሊከተው እንደሚችልም ሲተነብዩ ሰንብተዋል።

ሜርክል ወደ ስብሰባው ከመሄዳቸው በፊት ጀርመን ምንም ዓይነት ተጨማሪ ስደተኞችን እንዳይቀበሉ ግፊት ሲደረግባቸው ቆይቷል።

በኀብረቱ አገራት የተመዘገቡ ስደተኞች እያሉ ጀርመን አዳዲስ ስደተኞችን ተቀብሎ የማስተናገዷን ሐሳብ በርካታ የኅብረቱ አገራት ሲቃወሙት ሰንብተዋል።

የጀርመን ጣምራ መንግሥትን ከመሠረቱት ውስጥ አንዱ ሲኤስዩ ሜርከል በስደተኞች ላይ መጨከን ካልቻሉ ጥምረቱን እንደሚያፈርስ ሲዝት ነበር። ፓርቲው ከጥምረቱ ከወጣ ደግሞ የሜርክል መንግሥት የምክር ቤቱን ብዙኃን መቀመጫን ስለሚያጣ አገሪቱን ለመምራት ይቸገራል።

የሕገወጥ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ጉዞ አሁን አሁን እየቀነሰ መምጣቱ ተነግሯል። በ2015 ወደ አውሮፓ የሚገቡ ሕገወጥ ስደተኞች የኅብረቱን አገራት መጠኑ ከፍ ያለ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ጥሏቸው ቆይቷል።

ከዚያ ወዲህ ግን ወደ ኅብረቱ አገራት የሚገቡ ከለላ ፈላጊዎች ቁጥራቸው በ96 በመቶ እየቀነሰ መምጣቱ ይነገራል።

በዚህ ወር ጣሊያን ለስደተኞች ድጋፍ የሚሰጠውንና የሚታደገውን የጀርመን ግብረሰናይ መርከብ ወደ አገሯ እንዳይጠጋ ከከለከለች በኋላ በአገራት መካከል ከረር ያለ አለመግባባት ተከስቶ ነበር።

በመጨረሻም ስደተኞችን የሚታደገው መርከብ በማልታ መልህቁን እንዲጥል ዲፕሎማሳዊ ስምምነት ተደርሷል።

ኖርዌይም የተወሰኑ ስደተኞችን ለመቀበል ተስማምታለች።