በኢራን ታስረው የነበሩ የአሜሪካ ዜጎች በ6 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ተለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, ANYHOPEFORNATURE/FREETHE NAMAZIS/NEDASHARGHI
ለዓመታት በኢራን ታስረው የቆዩት አምስት የአሜሪካ ዜጎች ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ወደ አገራቸው እያመሩ ነው ተባለ።
አምስቱ ግለሰቦች ከእስር የተለቀቁት አሜሪካ ዜጎቿን ነጻ ለማውጣት ስትል እንዳይንቀሳቀስ አድርጋው የነበረው የኢራን 6 ቢሊዮን ዶላር እንዲለቀቅ በኳታር አደራዳሪነት ከተስማማች በኋላ ነው።
በዚህ ስምምነት መሰረትም የኢራንና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላቸው አራት ወንዶችና እና አንዲት ሴት በቻርተር አውሮፕላን ከቴህራን ወደ ኳታር መዲና መጓዝ ችለዋል።
ግለሰቦቹ ከከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር የተገናኙ ሲሆን አሁን ላይ ወደ ዋሽንግተን እየተጓዙ መሆኑ ተገልጿል።
ከኢራን እስር ቤት ነጻ ከወጡት አሜሪካውያን መካከል በቴህራን አደገኛ እስር ቤት ስምንት ዓመታት ገደማ ያሳለፈው የ51 ዓመቱ ሲያማክ ናማዚ፣ የ59 ዓመት የንግድ ሰው ኢማድ ሻርጊ እና ተጨማሪ የአንግሊዝ ዜግነት ያለው የ67 ዓመት የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ ሞራድ ታግባዝ ይገኙበታል።
አሜሪካ ዜጎቿ የታሰሩት መሠረተ ቢስ በሆነ ክስ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር ሲባል ነው ብላለች።
በአገራቱ መካከል በተካሄደው የመጀመሪያው የስምምነት አካል መሠረት ግለሰቦቹ ከእስር ቤት ቴህራን ወደሚገኝ ቤት የተዛወሩት ነሐሴ አጋማሽ ላይ ነበር።
የአሜሪካን ማዕቀብ በመጣስ ተከሰው በአሜሪካ እስር ቤት የሚገኙ አምስት ኢራናውያንም ምህረት ተደርጎላቸዋል።
እነዚህ እስረኞች ሬዛ ሳርሃንግፖር ፣ ካምቢዝ አታርካሻኒ፣ ካቬህ ሎትፎላህ አፍራሲያቢ፣ ሜህራዳድ ሞኤኒ አንሳሪ እና አሚን ሃዛንዛደህ በሚል ስም የሚታወቁ ሲሆን፣ሁሉም እስረኞች ወደ ኢራን ይመለሳሉ ተብሎ አይጠበቅም።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዜጎቹን የያዘው አውሮፕላን በዶሃ ሲያርፍ “ በኢራን ታስረው የነበሩ አምስት ሰላማዊ አሜሪካውያን ዛሬ ወደ አገራቸው እየመጡ ነው” ብለዋል።
ፕሬዚደንቱ አምስቱ ግለሰቦች ለዓመታት ስቃይና መከራን ታግሰዋል አልፈዋል ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚደንቱ በግለሰቦቹ እስር ላይ ተሳትፈዋል በሚል የቀድሞውን የኢራን ፕሬዚደንት ማህሙድ አህማዲንጃድ እና የኢራን የደኅንነት ሚኒስቴር ኢላማ ያደረገ አዲስ ማዕቀብ አስታውቀዋል።
ለስምንት ዓመታት ገደማ በእስር ያሳለፈው የ51 ዓመቱ ሲያማክ ናማዚ በሰጠው መግለጫ “ ዓለም እንድትረሳኝ ያልፈቀዳችሁ፣ ሁላችሁም ባትሆኑ ኖሮ ዛሬ ነጻ አልወጣም ነበር።“ ብሏል።
ሲያማክ ጨምሮም በእስር ላይ ሳለ ድምጽ ለሆኑት፣ ጥንካሬ ባጣ ጊዜ ብርታት ለሆኑት ሁሉ ምስጋና አቅርቧል።
እነርሱን ለማታደግ እንዲሁም የአሜሪካ ዜጎችን ከፖለቲካ በላይ በማስቀደም አስደናቂ እና አስቸጋሪ ውሳኔ በማሳለፋቸውም ፕሬዚደንት ባይደንን አሞካሽቷል።
አሜሪካ እና ኢራን እስረኞችን ለመለዋወጥ እንዲሁም እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት በኳታር አደራዳሪነት ከባለፈው ዓመት የካቲት ወር አንስቶ ለወራት የዘለቀ ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው።
ምንጮች እንደሚሉት በዶሃ ቢያንስ ለዘጠኝ ዙር ውይይት ተደርጓል። የኳታር ከፍተኛ ባለስልጣናትም በቴህራንና በዋሽንግተን መካከል ተመላልሰዋል።
በኳታር ጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እያገለገሉ የሚገኙት ትውልደ ኢራናዊው ፕሮፌሰር ሜህራን ካምራቫ “ ስምምነቱ ሁለቱንም አሸናፊ እንዳደረገ አስባለሁ“ ሲሉ አስተያየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ ወደ ምርጫ እያመሩ ያሉት ባይደን አሜሪካውያንን ከእስር አስለቅቀው ወደ አገራቸው መልሰዋል። ለኢራንም በአሜሪካ ታስረው የነበሩ ኢራናውያን እንዲለቀቁ ሆኗል። ከዚህም በተጨማሪ ታግዶ የነበረው 6 ቢሊዮን ዶላር ተለቋል። ይህም ትልቅ ድል ነው።”ብለዋል።
የኢራን ባለስልጣናት ገንዘባቸውን በሚፈልጉት ነገር ላይ እንደሚያውሉት በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ሆኖም በዚህ ስምምነት ውስጥ የተሳተፉ ምንጮች ገንዘቡ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበታል ብለዋል።
“ወደ ኢራን የሚሄድ ገንዘብ አይኖርም። ምግብ፣ መድሃኒት፣ ግብርና እና የሦስተኛ ወገን ክፍያን ጨምሮ የሰብዓዊ ግብይቶች ብቻ የሚፈፀምበት ነው” ብለዋል።
ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህ ገንዘብ በአሜሪካ ማዕቀብ የታገደ የኢራን ንብረት አካል አልነበረም።
በደቡብ ኮሪያ ያለው ገንዘብ፣ ከኢራን የነዳጅ ዘይት ሽያጭ የተገኘ ገቢ ሲሆን ለቴህራን የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ከማዕቀብ ነጻ የሆነ ድጋፍ ለማድረግ የተቀመጠ ነው፤ ነገር ግን የገንዘብ ምንዛሬ ችግሮችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ወጪ አልተደረገም።
ኢራን በመላው ዓለም ከነዳጅ ሽያጭ ማግኘት የነበረባትን ገንዘብ ሳትሰበስብ እአአ 2018 ላይ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምዕራባውያኑ ከኢራን ጋር ደርሰውት የነበረውን የኒውክለር ስምምነት ጥለው መውጣታቸው ተከትሎ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ሳይከፈላት ቀርቷል።
ይህ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ውሳኔ በተቃዋሚዎቹ ሪፓብሊካኖች በኩል ትችት ገጥሞታል።
የሪፓብሊካን የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባል ማይክል ማክኮውል፣ የባይደን አስተዳደር “በዓለም ላይ ሽብር በመደገፍ ለሚታወቅ መንግሥት የእገታ ማስለቀቂያ ገንዘብ እና የማዕቀብ እፎይታ እየሰጠ ነው” ሲሉ ውሳኔውን ተችተዋል።












