ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ በኬንያ ታሪክ እጅጉን የተጠሉ መሪ ናቸው?

የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዊልያም ሩቶ ፕሬዝዳንት ከሆኑበት ጊዜ አንስቶ እየጨመረ የመጣ የህዝብ ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ወደ ሥልጣን የመጡት፤ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል የገቡትን ቃል እንደሚፈጽሙ ተስፋ ባደረጉት የሀገሪቱ ነዋሪዎች የጉጉት እና ተስፋ ማዕበል ታጅበው ነበር።

አሁን ግን ፕሬዝዳንቱ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው የሚመስል የማያባራ ተቃውሞ እየገጠማቸው ነው።

በሁኔታው የተበሳጩ የሚመስሉት ሩቶ፤ እንዲህ ዓይነቱ የሕዝብ ቁጣ ለምን እንደ ዳንኤል አራፕ ሞይ እና ሌሎች አወዛጋቢ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ላይ እንዳልቀረበ ጠይቀዋል።

ሩቶ የጠቀሷቸው ዳንኤል አራፕ ሞይ ሀገሪቱን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ በፖለቲካ ጭቆና እና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስር አድርገው የገዙ አምባገነን መሪ ናቸው።

ረቡዕ ዕለት ሩቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በለጠፉት ጽሁፍ፤ "ይህ ሁሉ ትርምስ ለምን [የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች] በሞይ፣ በሙዋይ ኪባኪ፣ በኡሁሩ ኬንያታ ላይ አልተደረገም? ንቀት እና እብሪት ለምን?" ሲሉ ጠይቀዋል።

ተንታኞች፤ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ100 በላይ ሰዎች የተገደሉበትን ፕሬዝዳንት ሩቶ ላይ የተነሳ የሕዝብ ቁጣ "ያልተለመደ"፤ ኬንያውያንን ከብሔር፣ ከሃይማኖት እና ከመደብ ክፍፍል ባሻገር አንድ ያደረገ ሲሉ ይገልጹታል።

በሩቶ አስተዳደር ላይ ተቃውሞ መሰማት የጀመረው ወደ ሥልጣን ከመጡ አንድ ዓመት እንኳ ሳይሞላ ነው። ከሦስት ዓመታት በኋላ ብዙ የተበሳጩ ኬንያውያን ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚፈልጉ ሲሆን ለዚህም "ሩቶ መልቀቅ አለበት እና "ሩቶ ለአንድ የሥልጣን ዘመን" በሚሉ መፈክሮች የሚመራ የማያቋርጥ የተቃውሞ ሰልፍ እያካሄዱ ነው።

ሩቶ ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ራሳቸውን ያቀረቡት በድህነት እና በጽናት የታጀበ የልጅነት ጊዜን እንዳሳለፈ ተራ ሰው አድርገው ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዶሮ ሻጭነት ተነስቶ ፕሬዝዳንት መሆን እንደሚቻል በመጥቀስም ጭምር የተራውን ዜጋ ልብ ለመግዛት ጥረት አድርገዋል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አንድ ጋዜጣ ሩቶ "በኬንያ እጅጉን የተጠላው ፕሬዝዳንት" እንደሆኑ የሚጠይቅ አርዕስት ይዞ በወጣበት ወቅት ይህንን ስሜት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እና በሕዝብ ንግግሮች ላይም ተንጸባርቋል።

ይህ ሁኔታ ብዙውን ጊዜ በብሔር ታማኝነት እና በመደብ መከፋፈል ታጥሮ በሚታየው የኬንያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ ክስተት ነው።

ሩቶ የፕሬዝዳንትነት ሩጫውን ለማሸነፍ የተጋረጡባቸውን መሰናክሎች ሲሻገሩ እንደታየው ሁሉ፤ አሁን ተመሳሳይ አካሄድ በፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ ላይ ተግባራዊ እየሆነ ይመስላል።

በዚህ ሳምንት ወጣቶች የኬንያን ፖለቲካ ለረጅም ጊዜ አንቆ የያዘው የብሔር ክፍፍልን እንደገና ለማነሳሳት የተደረጉ ሙከራዎችን ውድቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ "ሁላችንም ኪኩዩዎች ነን" የሚለው ሐረግ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች በሰፊው ሲሠራጭ ሰንብቷል።

"ሁላችንም ኬንያውያን ነን" ለሚለው ምላሽ የሚመስል ተቃራኒ ትርክት ብቅ ቢልም ተመሳሳይ ተቀባይነት ማግኘት አልቻለም። አንዳንዶች በመጀመሪያው መልዕክት ውስጥ ያለውን የአብሮነት ስሜት ለመከፋፈል የተደረገ ሙከራ አድርገው ተመልክተውታል።

በማውንት ኬንያ አካባቢ የሚገኙት እና በኬንያ ትልቁ ብሔረሰብ የሆኑት ኪኩዩዎች፤ በ2022 ምርጫ የክልሉ ተወላጅ የሆኑትን ሪጋቲ ጋቻጓን ምክትል ፕሬዝዳንት አድርገው የተወዳደሩትን ሩቶን አብዝተው ደግፈዋል።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት ጋቻጓ ክህደት ሲሉ በገለጹት በውዝግብ የተሞላ ክስ (ኢምፒችመንት) ከሥልጣን መባረራቸው በአካባቢው አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ይህንን ተከትሎ የሩቶ ደጋፊ የሆኑ አንዳንድ ፖለቲከኞች የኪኩዩ ልሂቃንን በፕሬዝዳንቱ ላይ ተቃውሞ እንዲቀጣጠል በማድረግ ከስሰዋል።

የፖለቲካ ተንታኙ ማርክ ቢቻቺ፤ በፕሬዝዳንቱ ላይ የተነሳው ተቃውሞ በዘር የተመሠረተ ሳይሆን በከተሞች እና በገጠር አካባቢዎች በሚገኙ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ የተፈጠረ ስሜት እንደሆነ ይናገራል።

"በፕሬዝዳንቱ እና በአገዛዙ ላይ የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ"፤ "ከዚህ በፊት ያልታየ" እና "ታሪካዊ" በማለት የሚገልጸው የፖለቲካ ተንታኙ፤ የአሁኑ ሁኔታ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞይ ሀገሪቱን በአንድ ፓርቲ ሥርዓትን ሲመሩ በነበረበት ጊዜ በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ ከታዩት ፖለቲካዊ አመጾች እንኳ እንደሚበልጥ ይናገራል።

የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳን ዳንኤል አራፕ ሞይ ካጀቧቸው የክብር ዘቦች ጋር በመሆን በግራ እና በቀኝ በተደረደሩ የክብር ዘቦች መካከል ሲራመዱ

የፎቶው ባለመብት, Gamma-Rapho via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እንደ ዳንኤል አራፕ ሞይ ያሉ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንቶችም ከፍተኛ ተቃውሞ አጋጥሟቸው ነበር

ያ ጊዜ አሰቃቂ እርምጃዎች የተወሰዱበት እና የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ሥርዓት ለማምጣት ደም አፋሳሽ ትግል የተደረገበት ነበር።

የፖለቲካ ተንታኙ ቢቻቺ ግን ምንም እንኳ በወቅቱ የነበረ ሁኔታ አስከፊ ቢሆንም ሩቶ እየተጋፈጡት ያለውን ዓይነት ጫና በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ እንዳላስከተለ ይገልጻል።

በዚያን ጊዜ የነበረው ውጥረት ከቀዝቃዛው ጦርነት ጋር የተገናኘ እና በመላ አህጉሪቱ ሲስተዋል የነበረ እንደሆነ ያስረዳል።

ምሁሯ ዶ/ር ንጆኪ ዋማይ ግን አሁን ፕሬዚዳንቱ ያጋጠማቸው ችግር በቀውስ ጊዜያት የሚፈጠር የፖለቲካ ባህል አካል እንጂ ያልተለመደ ነገር እንዳልሆነ ትከራከራለች።

"ሁሉም ፕሬዚዳንቶች ከሕገ መንግሥቱ፣ ከኬንያ ሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ ሲጓዙ ነበር፤ ሁሌም በርካታ ብዙ ትችቶች አጋጥሟቸዋል" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

እንደ የመጀመሪያው የኬንያ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬንያታ እንዲሁም እንደ ተተኪያቸው ሞይ ያሉ፤ በወሳኝ ጊዜያት ከፍተኛ ተቃውሞ እና የሕዝብ አመኔታ ማጣት ያጋጠማቸው የቀድሞ መሪዎችን በማሳያነት ትጠቅሳለች።

በኬንያታ ጊዜ የቁልፍ የፖለቲካ መሪዎች ግድያ የተፈጸመ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ1982 ደግሞ ሞይ ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተካሂዷል።

"[በዚህ ጊዜ] የተለየ ነገር፤ መረጃ የሚሠራጭበት መጠኑ ከፍ ያለ መሆኑ ነው" ትላለች። ዲጂታል እውቀት ያላቸው የኬንያ ወጣቶች ተጽዕኖን በመጥቀስ፤ የማኅበራዊ ሚዲያ እና የዲጂታል መሳሪያዎች ሰፊ ተደራሽነት የሕዝብ ንግግርን እንዲጎላ ማድረጉን ታስረዳለች።

ሩቶ ሁሌም "በጣም ወግ አጥባቂ" እንደሆኑ የምትናገረው ዶ/ር ንጆኪ፤ ይህ የፖለቲካ አመለካከት በበርካታ ኬንያውያን በተለይም በወጣቶች ዘንድ ተቀባይነት ካላቸው የሊበራል እሴቶች ጋር የሚጋጭ መሆኑን ታነሳለች። ይህ የሃሳብ ልዩነት እየጨመረ ላለው ውጥረት አስተዋጽኦ ማድረጉን በመጥቀስም ትከራከራለች።

የአሁኑ የተቃውሞ ዘመቻዎች በአብዛኛው በወጣቶች የሚመሩ፣ በይነ መረብ ላይ የተመሠረቱ፣ ያልተማከለ እና መሪ የሌላቸው ተደርገው የሚታዩ እንዲሁም በአብዛኛው መሠረት ከያዘው የፖለቲካ መደብ ውጪ በሆነ አኳኋን እየተካሄዱ ያሉ ናቸው።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በኑሮ ውድነት፣ በከፍተኛ ግብር፣ በሙስና እና በፖሊስ ጭካኔ ምክንያት በቁጣ ተነስተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ግን ሰሞነኛውን አለመረጋጋት የሚያቀጣጥሉት የብሔር ፖለቲካ እና ቅስቀሳዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ረቡዕ ዕለት "የብሔር ክፍፍልን፣ ጥላቻን፣ ኩራትን እና ንቀትን እናቁም። ሁላችንም ኬንያውያን ነን" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን "አስፈላጊውን ሁሉ" እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል። ፖሊስ የንግድ ተቋማትን ዒላማ ያደረጉ ሰልፈኞችን ከመግደል ይልቅ እግራቸው ላይ እንዲተኩስ አዘዋል። እነዚህ የፕሬዝዳንቱ አስተያየቶች ቁጣ እና ስላቁን አባብሰውታል።

ሁለት ፖሊዎች ተቃውሞ ባለበት መንገድ ላይ ቆመው፤ አንዱ ፖሊስ ወደ ላይ እየተኮሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፖሊስ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማፈን ከመጠን በላይ ኃይል በመጠቀም ይከሰሳል

ካለፈው ዓመት ወዲህ የኬንያ መንግሥት ለሚነሱበት ተቃውሞዎች እና የተቃርኖ ሀሳቦች ምላሽ የሰጠው የጅምላ አስከፊ እርምጃዎችን በመውሰድ ነው። የጅምላ እስሮች የተፈጸሙ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች በፀጥታ አካላት ታፍነው እንደተወሰዱም ተነግሯል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች፤ ይህ ስልት የሕዝብን ቁጣ ከማባባስ አልፎ ዜጎች ከመንግሥት እንዲርቁ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። ፖሊስ ተቃውሞውን ለማፈን ከመጠን በላይ ኃይል ተጠቅሟል የሚል ክስም ያቀርባሉ።

ካለፈው ዓመት ሰኔ ጀምሮ በተከታታይ በተደረጉ ፀረ መንግሥት ተቃውሞዎች ላይ ከ100 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ባለፈው ሳምንት ሰኞ በተደረገው ተቃውሞ 38 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ይህም ከእስካሁን ተቃውሞዎች ሁሉ ብዙ ሰዎች የተገደሉበት እጅግ አስከፊ ቀን አድርጎታል።

የተፈጸሙት ግድያዎች ፖሊስ ላይ ሪፎርም እንዲደረግ ወይም ሰልፈኞችን ለማረጋጋት ጥረት እንዲደረግ ምክንያት ከመሆን ይልቅ፤ ሐዘንን ወደ ቁጣ በመለወጥ ቀጣይ ተቃውሞዎችን ለማቀጣጠል ያገለግላሉ።

መንግሥት ለተፈጠረው አመጽ ተጠያቂ የሚያደርገው ተቃዋሚዎችን ሲሆን፣ ሰልፈኞችን ፖሊስ ጣቢያዎችን በማጥቃት እና መፈንቅለ መንግሥት በማካሄድ ከስሷል።

የፖለቲካ ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያው ዶ/ር ሄዝቦን ኦዊላ፤ አመጹን በኬንያ ታሪክ "በአንድ አገዛዝ ላይ የተፈጸመ እጅግ ከፍተኛ የሆነ አመፅ ሊሆን እንደሚችል" ይናገራል። በሁሉም የሕይወት መስመር ላይ የነበሩ ሰዎችን ለተቃውሞ ወደ አንድነት እንዳመጣም ያክላል።

የዚህ ቁጣ አንዱ ምክንያት ፕሬዝዳንቱ ከሕዝቡ ጋር የሚነጋገሩበት መንገድ እንደሆነ ይጠቅሳል። ሩቶ የተራውን ዜጋ ገቢ ከፍ ለማድረግ የገቡት ቃል "እውነተኛ፣ እጅግ በጣም እውነተኛ" እንደነበረ እና የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻውን ከብሔር ወደ መሠረታዊ ችግሮች ከፍ አድርገውት እንደነበር ይናገራል።

"ከዚያም ፕሬዝዳንት ሆነ። እስከአሁን እየጠበቅን ነው። ኬንያውያን የከፋ ነገር እያጋጠማቸው ነው" ሲል በኬንያውያን ዘንድ የተፈጠረውን ጥልቅ የመከፋት ስሜት በማንሳት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሩቶ፤ እንዳለፉት መንግሥታት ጥንቃቄ የተሞላበት ቃል ከመግባት ይልቅ አሁንም ትላልቅ ቃሎችን እየገቡ መቀጠላቸው፤ ተስፋን ወደ መሸርሸር እንደሚያመራ ያነሳል። "ቁጣውን እየፈጠረ ያለው የተስፋ መቁረጥ ስሜት ነው" ይላል።

የአትክል መደብር ደጅ ላይ ቁጭ ያለች ሻጭ

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሩቶ የመደበኛውን ዜጋ ፍላጎት ለማሳካት ቃል ገብተው ነበር

በተቃዋሚዎች ላይ ተኩስ እንዲተኮስ የተሰጠውን ትዕዛዝ በምሳሌነት የሚጠቅሰው ዶ/ር ሄዝቦን፤ ፕሬዝዳንቱ ብዙውን ጊዜ ዝምታ የተሻለ ዕድል በሚሰጣቸው ጊዜ ላይ ይናገራሉ ይላል። ይህም ራሳቸውን ከመጠን በላይ እንዲያጋልጡ እና ሳያስቡት ከባድ ብሔራዊ ጉዳዮችን እንደ ግል ጉዳይ እንደወሰዱት እንዲሰማ እንደሚያደርግ ያነሳል።

በዚህም የተነሳ፤ የሚነሱ ትችቶች በአስተዳደር ሥርዓት ውድቀት ላይ ከማተኮር ይልቅ በቀጥታ ወደ ፕሬዝዳንቱ ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉን ይጠቅሳል።

ሩቶ፤ ግዙፉን የተመጣጣኝ የቤቶች ፕሮጀክት፣ ሁሉን አቀፍ የጤና ሥርዓት፣ የዲጂታል ሥራዎች ፈጠራ እና በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ፕሮግራምን እንደ ቁልፍ ስኬት በመጥቀስ አስተዳደራቸው የኬንያውያንን ኑሮ ለማሻሻል ያደረገውን ጥረት በተደጋጋሚ በአጽንኦት ያነሳሉ።

ከቀናት በፊት በአንዱ የመኖሪያ ቤት ግንባታ በሚካሄድበት ቦታ ላይ ጉብኝት ለማድረግ በተገኙበት ወቅት፤ የወጣቶች ሥራ አጥነትን ከባድ ችግር መሆኑን አምነዋል፤ ነገር ግን የችግሩ ከእርሳቸው የፕሬዝዳንትነት ዘመን በፊት የተፈጠረ ስለመሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንቱ፤ ችግሩን ለመፍታት ጊዜ ስለሚወስድ ትዕግስት እንዲኖር ጠይቀዋል። ነገር ግን የኑሮ ውድነት፣ እውን ያልሆኑ ቃል ኪዳኖች እና ተስፋ መቁረጥ እየጨመረ የመጣባቸው ብዙዎቹ ኬንያውያን ትዕግስት ማድረግ የሚችሉት ነገር አይደለም።

አንዳንዶቹ የፕሬዝዳንቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ኬንያውያንን ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላሉ። በፕሮጀክቶቹ ምክንያት የ1.5 በመቶ የቤት ግብር እና የ2.75 በመቶ የጤና መድኅን ታክሶች ከኬንያውያን ደመወዝ ላይ ይቀነሳል።

ከፍተኛ ግብር መጣሉ የተሻለ የሕዝብ አገልግሎትን አላመጣም የሚል ግንዛቤ ባለበት በዚህ ወቅት፤ እነዚህን ከፍተኛ ግብሮች የመክፈል ሕመም በዕለት ተዕለት ውይይቶች ላይ ገዝፎ ይታያል።

ዶ/ር ኦዊላ፤ እንደ ሁሉን አቀፍ የጤና ጥበቃ ፕሮጀክት ያሉ አንዳንድ ጅምሮች ከፍተኛ ውጤት እንዳላቸው እና ሌሎቹ ፕሮጀክቶች በጊዜ ሂደት ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይናገራል።

የፖለቲካ ተንታኙ ማርክ ቢቻቺ ግን መንግሥት "ሰዎች ምን እንደሚሰማቸው የማወቅ አቅም አጥቷል" በማለት ይከራከራል። የሕዝብ ቅሬታ እየጨመረ ቢመጣም የመንግሥት አካሄድ አለመለወጡን ይጠቅሳል።

በሕዝቡ እና በፕሬዝዳንቱ መካከል ያለው "የፍቅር-ጥላቻ ግንኙነት" እንደሆነ የሚገልጸው ቢቻቺ፤ የመንግሥትን አካሄድ በመጥቀስ ጉዳዩ የሚለወጥ አይመስልም ይላል።

ፕሬዝዳንቱ በአንድ ወቅት "በኬንያ የበዛ አድናቆት እና ውዳሴ ከተቸራቸው መሪዎች" መካከል አንዱ እንደነበሩ እና አሁን ግን ከፍተኛ ቁጣ እንደተቀሰቀሰባቸው በመጥቀስ "እንዴት ራሳችንን እዚህ መንገድ ላይ አገኘነው" ሲል ይጠይቃል?