አወዛጋቢው ኡጋንዳዊ ጄኔራል ከሥልጣናቸው ተነሱ

የፎቶው ባለመብት, Muhoozi Kainerugaba/twitter
አወዛጋቢው የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ልጅ ሌፍተናንት ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ ከአገሪቱ የምድር ጦር ኃይል አዛዥነት ሥልጣናቸው ተነሱ።
የፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ሙሆዚ ካይኒሩጋባ ከነበራቸው ሥልጣን ይነሱ እንጂ፣ ወደ ሙሉ ጄኔራልነት እንዲያድጉ ተደርገዋል። ይህም በአገሪቱ ሠራዊት ውስጥ ከፍተኛ የማዕረግ ደረጃ ነው ተብሏል።
ጄኔራል ሙሆዚ ከምድር ጦር አዛዥነታቸው ጎን ለጎን ደርበው ይዘውት የነበረውን የልዩ ዘመቻዎች የፕሬዝዳንቱ አማካሪነት ቦታቸውን እንደያዙ ይቀጥላሉ።
ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ ቀደም ሲል የአባታቸው የዩዌሪ ሙሴቪኒ ጥበቃን የሚያካሂደው ልዩ ኃይል አዛዥ ነበሩ።
ጄኔራሉ ኡጋንዳ በሶማሊያ ውስጥ ያሰማራችውን ሠራዊት የመሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የሚካሄደውን በኡጋንዳ አማጺ ቡድን ላይ የሚካሄደውን ዘመቻ ሲመሩ ቆይተዋል።
ጄኔራሉ ከሚመሩት የምድር ጦር ኃይል አዛዥነታቸው የተነሱት ባለፉት ቀናት በትዊተር ላይ ካሰፈሯቸው አወዛጋቢ መልዕክቶች ጋር ስለመያያዙ የታወቀ ነገር የለም።
ትናንት ሰኞ ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ በትዊተር ላይ ሠራዊታቸው የጎረቤት አገር ኬንያን ዋና ከተማን ለመቆጣጠር ሁለት ሳምንት ብቻ እንደሚበቃው አስፍረው በኬንያውያን ዘንድ ቁጣን ቀስቅሰዋል።
ይሁን እንጂ ማክሰኞ ዕለት ጠዋት ጄኔራል ሙሆዚ፣ ከአባታቸው ከፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ጋር እንደተነጋገሩ እና በትዊተር ገጻቸው ላይ የሚያጋሩት ጽሁፍ በኬንያ ውዥንብር እንደፈጠረ እንደተረዱ ገልጸው፣ ፕሬዝዳንቱ ለውጦች እንደሚኖሩ እንዳሳወቋቸው ተናግረዋል።
ነገር ግን ጄኔራሉ “ለውጥ” ያሉት በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ስለሚደረገው ሹም ሽር ማለታቸው ስለመሆኑ በግልጽ አላብራሩም።
የኡጋንዳ መንግሥት፣ የፕሬዳንቱ ልጅ በተከታታይ በትዊተር ገጻቸው ላይ በሚለቋቸው ጽሁፎች ከተቀሰቀሱ ውዝግቦች ራሱን አርቋል።
የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መንግሥት ማኅበራዊ ሚዲያን የተመለከተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንዳላዘጋጀ ገልጾ፣ ኡጋንዳ ከኬንያ ጋር ያላትን ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከፍ አድርጋ እንደምትመለከተው ገልጿል።
ጨምሮም ሁለቱ አገራት የጋራ ታሪክ ያላቸው፣ አንዳቸው ለአንዳቸው ሉዓላዊነት ክብር፣ እምነት እንዲሁም አንድ የሆነ የምሥራቅ አፍሪካን ማኅበረሰብ የመገንባት ፍላጎት እንዳላቸውም በመግለጫው አመልክቷል።
የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ፌሊክስ ኩላይዬ በበኩላቸው ኡጋንዳ ከኬንያ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላት በመግለጽ፣ የኡጋንዳ ጦር ጎረቤት አገር ኬንያን ሊወር እንደማይችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ልጅ ጄኔራል ሙሆዚ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሆኑ አነጋጋሪ ጽሁፎችን በትዊተር ገጻቸው ሲያጋሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
ቀደም ብሎ የትግራይ አማጺያንን እንደሚደግፉ የገለጹ ሲሆን፣ በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።












