የአጼ ኃይለ ሥላሴ መገልገያዎች ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ለዕይታ ሊቀርቡ ነው

የፎቶው ባለመብት, BATH & NORTH EAST SOMERSET COUNCIL
አጼ ኃይለ ሥላሴ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በስደት ላይ በቆዩበት ጊዜ የነበሯቸው ንብረቶች ለሕዝብ ዕይታ ሊቀርቡ ነው።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጣሊያን ወረራን ተከትሎ ለተወሰኑ ዓመታት ብሪታኒያ ውስጥ በምትገኘው ባዝ ውስጥ መቆየታቸው ይታወቃል።
በዚህ ጊዜም ይጠቀሙባቸው የነበሩ የጎልፍ መጫወቻዎች እና ከዘራቸውን ጨምሮ ሌሎችም የግል መገልገያዎቻቸው በሮማን ባዝ ሙዚየም ውስጥ የነገሥታት ክፍል ከጥቅምት 14/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለዕይታ ይቀርባሉ።
ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከአውሮፓውያኑ 1936 አስከ 1941 ድረስ ባዝ ውስጥ በሚገኘው ፌይርፊልድ ሐውስ በተባለ ስፍራ በስደት ቆይተዋል።
በተጨማሪም የኖሩበት ፌይርፊልድ ሐውስ በጥቅምት ወር በየሳምንቱ እሁድ በአስጎብኚዎች አማካይነት የጉብኝት ፕሮግራም አዘጋጅቷል።
ፌይርፊልድ ሐውስ የተባለው የዚህ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ የሆነው ራስ ቤንጂ፣ ለዕይታ ከሚቀርቡት የንጉሡ መገልገያዎች መካከል አንዳንዶቹ አገራቸውን ነጻ በማውጣት በኩል በተደረገው ጥረት ውስጥ ፖለቲካዊ ሚና የነበራቸው ናቸው ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, FAIRFIELD HOUSE CIC
የንጉሰ ነገስቱ ከዘራ የነበረውን ወሳኝ ሚናን ራስ ቤንጂ ሲያስረዳም፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አገራቸው በጥቃት ስር በነበረችበት ወቅት ላደረጉት የእግር ጉዞ በእጅጉ ጠቅሟቸዋል ይላል።
“ንጉሰ ነገስቱ በመላዋ ባዝ በእግራቸው ይጓዙ ነበር” ከመኖሪያቸው ተነስተው በከተማዋ ውስጥ ያሉ ስፍራዎችን በማቆራረጥ በየዕለቱ ይዘዋወሩ እንደነበር ራስ ቤንጂ ገልጿል።
“ከጣሊያኖች ጋር ጦርነት ውስጥ ከተገባ በኋላ፣ ንጉሡ ከአሰቃቂ ሁኔታ በኋላ በሚከሰት ሁኔታ ይሰቃዩ ነበር። ከኢትዮጵያ ይሰሙ በነበሩት ተከታታይ አሰቃቂ ዜናዎች የተነሳ በስደት ላይ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ጊዜው በእጅጉ ጨለማ ነበር” ብሏል።
ራስ ቤንጂ ጨምሮም የግርማዊነታቸው ቅርስ በዩናይትድ ኪንግደም የጥቁሮች ታሪክ ውስጥ እጅግ ጉልህ ቦታን ይይዛል ሲል ተናግሯል።
ይህ የአሁኑ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መገልገያዎችን ለዕይታ የማብቃት ተግባር “ንጉሡ በባዝ ከተማ ውስጥ ያኖሩትን ቅርስ ለማሳወቅ ለዓመታት የሚከናወን ሥራ አንድ አካል ነው” ሲል አክሏል።
የአጼ ኃይለ ሥላሴን መገልገያዎችን ለዕይታ ከማቅረብ ባሻገር፣ ማንኛውም ሰው በአስጎብኚዎች በመመራት የንጉሡን የቀድሞ መኖሪያ ቤት የውስጥ ክፍል መጎብኘት ይችላሉ።
በዚህም በቤቱ ውስጥ እና ከውጪ ያሉ ስፍራዎች በአጼ ኃይለ ሥላሴ ቆይታ ወቅት ያላቸውን ቦታና ታሪክ የመረዳት ዕድልን ይፈጥርላቸዋል ተብሏል።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጣሊያን የአምስት ዓመታት ወረራ ካበቃ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው በወታደሮቻቸው ከሥልጣን እስከተወገዱበት ጊዜ ድረስ ለረጅም ዓመታት ኢትዮጵያን በንግሥና መርተዋል።












