ዕጽ አዘዋዋሪ ታጣቂዎች በሜክሲኮ የአንድ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ 18 ሰዎችን ገደሉ

የፎቶው ባለመብት, TOTOLAPAN GOVERNMENT
የዕጽ አዘዋዋሪ ታጣቂዎች አንድ የሜክሲኮ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ ቢያንስ 18 ሰዎችን መግደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
በተጨማሪም ታጣቂዎቹ አስቀድመው የከንቲባውን አባት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ መግደላቸውም ተዘግቧል።
ታጣቂዎቹ ረቡዕ እለት የሳን ሚጉዌል ከተማ ምክር ቤት አዳራሽን ጥሰው በመግባት ነው ጥቃቱን የፈጸሙት። ከጥቃቱ በኋላ በበይነ መረብ የተሰራጩ ፎቶዎች በጥይት የተባሳሳ የአዳራሹ ግድግዳዎችን አሳይተዋል።
የተገደሉት ከንቲባ ኮንራድ ሜንዶዛ አልሜዳ አባል የሆኑበት ግራ ዘመሙ ፒአርዲ የተባለው ፓርቲ፣ ግድያውን “የፈሪዎች ድርጊት” በማለት አውግዞ ፍትህ ጠይቋል።
በሜክሲኮ ውስጥ እጅግ ኃያል ከሆነው የዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው ሎስ ቴኩይሌሮስ የተባለው የወንጀል ቡድን ጥቃቱን ፈጽሟል ተብሎ ይከሰሳል።
በከተማዋ አዳራሽ ውስጥ በታጣቂዎቹ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ፖሊሶች እና የከተማው ምክር ቤት ሠራተኞች የተገደሉ ሲሆን፣ ግድያውን የሚያሳዩ አሰቃቂ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት እየተሰራጨ ነው።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ ወደ ከተማዋ ምክር ቤት አዳራሽ ከመሄዳቸው በፊት የከንቲባው አባት የሆኑትን የቀድሞውን ከንቲባ ሁዋን ሜንዶዛ አኮስታን በቤታቸው ውስጥ ገድለዋል።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ ግድያውን በሚፈጽሙበት ጊዜ ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ድጋፍ ለመስጠት ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ ለማድረግ ዋና የተባለውን አውራ ጎዳና በከባድ ተሽከርካሪ ዘግተውት ነበር።
በጎሬሮ ግዛት ውስጥ በወንጀለኛ ቡድኖች የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የሚያጋጥሙ ሲሆን፣ የአሁኑ ግን እጅግ የከፋው እንደሆነ ተነግሯል።
ጥቃቱ የተፈጸመባት ሳን ሚጉዌል ቶቶላፓን በኃይለኛ የዕጽ አዘዋዋሪ ቡድኖች ቁጥጥር ስር በሚገኘው በምዕራባዊ ሜክሲኮ ውስጥ ያለች ከተማ ናት።
ይህ አካባቢ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚታፈስበትን የዕጽ ዝውውር ለመቆጣጠር የተለያዩ የወሮበላ ቡድኖች ፍልሚያ የሚያደርጉበት ነው።
ጥቃቱን ተከትሎ ታጣቂዎቹን ለማደን የባሕር እና የምድር ኃይል አባላትን ማሰማራቱን የሜክሲኮ መከላከያ ሚኒስቴር ኣሳውቋል።
ጥቃቱ ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ የሎስ ቴኩይሌሮስ ቡድን አባል ናቸው የተባሉ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰራጩት ቪዲዮ፣ ቡድኑ ተቀናቃኛቸውን ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድንን ሲፋለሙበት ወደነበረው ክልል መመለሳቸውን ገልጸው ነበር።
ይህ የወንጀለኛ ቡድን መሪው ራይቤል ጃኮቦ ዴ አልሞንቴ አስኪገደል ድረስ በአውሮፓውያኑ 2015 እና 2017 በአካባቢው ያሉ የተለያዩ ከተሞችን ከንቲባዎች በማስፈራራት ከባድ ቀውስን አድርሷል።
የወሮበሎቹ ቡድን መሪ የነበረው ዴ አልሞንቴ፣ ከሚጠጣው ተኪላ ከተባለው የአልኮል መጠጥ የተነሳ “ኤል ተኪሌሮ” ወይም “ተኪላ ጠጪው” በሚል ስያሜ ይታወቅ የነበረ ሲሆን፣ ቡድኑም ለመጠሪያው ይህንን ስም ወርሷል።












