ጠ/ሚንስትሯ በመኖሪያ ቤታቸው ሁለት ሴቶች ከፊል እርቃናቸውን ፎቶ ከተነሱ በኋላ ይቅርታ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፊንላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን በመኖሪያ ቤታቸው ሁለት ሴቶች ከወገባቸው በላይ እርቃናቸውን ሆነው ፎቶግራፍ ከተነሱ በኋላ ይቅርታ ጠየቁ።
በጠቅላይ ሚኒስትሯ ቤት ካናቴራ ሳይለብሱ እየተሳሳሙ ፎቶ የተነሱት ሁለት ሴቶች ተዋቂ ሰዎች ናቸው ተብሏል።
ሁለቱ ሴቶች ፎቶውን የተነሱት ባለፈው ሐምሌ በጠቅላይ ሚኒስትሯ ቤት በእንግድነት ተጋብዘው ሳለ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ባለፈው ሳምንት ሲደንሱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል መውጣቱን ተከትሎ ወቀሳ በዝቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።
የአደንዛዥ እፅ ምርመራ እንዲያደርጉ ተጠይቆ፣ እጽ አለመውሰዳቸው ተረጋግጧል።
የሁለቱ ዕውቅ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ሴቶች ፎቶ በስፋት በማኅበራዊ ሚዲያ ተዘዋውሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ “ፎቶዎቹ አግባብ አይደሉም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ እንዳሉት ሐምሌ ላይ ከሩስሮክ የሙዚቃ ፌስቲቫል በኋላ ሄልሲንኪ በሚገኘው ቤታቸው ድግስ አዘጋጅተው እንደነበረና ፎቶውም ድግሱ ላይ እንደተነሳ ተናግረዋል።
ፎቶው የተነሳው ለእንግዶች በተዘጋጀ መጸዳጃ ቤት እንደሆነ የፊንላንድ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የድግሱ ቪድዮ
አንድ ሌላ ፓርቲ ላይ ሲጨፍሩ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ከወጣ በኋላ የፓርቲያቸው አባሎች እንዲሁም ተቀናቃኞቻቸውም ትችት እየሰነዘሩ ነው።
በፓርቲው ላይ አደንዛዥ እፅ ወስደው ሊሆን ይችላል ያሉ አንድ ተቀናቃኝ ፖለቲከኛ ጠቅላይ ሚኒስትሯ እንዲመረመሩ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ የተወሰነ አልኮል ከመጠጣታቸው ውጪ ድግሱ ላይ አደንዛዥ እፅ እንዳልወሰዱና ወስደውም እንደማያውቁ ተከራክረዋል።
ምርመራ ከተደረገላቸውም በኋላ ከአደንዛዥ እፅ ነጻ ሆነው ተገኝተዋል።
ፊንላንውያን ምን ይላሉ?
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አኒካ ሳሪኮ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሯ ቤት የተነሳው ፎቶ በኑሮ ውድነት የሚንገላቱ የፊንላንድ ዜጎችን ሕይወት እንደማይወክል ገልጸዋል።
ሆኖም ግን የሰዎችን የሞራል ዝቅታም ይሁን ከፍታ መተንተን “ቦታዬ አይደለም” ብለዋል።
ፊንላንድ ከሩሲያ የሚጓዙ ቱሪስቶች ላይ እንደ አብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት ገደብ ጥላለች።
ጠቅላይ ሚኒስትሯን ዝነኛ እያደረጋቸው የመጣው ግን ከፖሊሲያቸው በላቀ የአኗኗር ዘያቸው ሆኗል።
ፊንላንዳውያን ስለ መሪያቸው የተደበላለቀ ስሜት አላቸው።
ተራው የፊንላንድ ዜጋ፣ ጠቅላይ ሚኒስሯ እንደ ማንኛውም በእሳቸው የዕድሜ ክልል ያለ ሰው ዘና ማለታቸውን ይደግፋል።
ጫና ከሚበዛበት ሥራቸው ውጪ መደነስና መዝናናት መውደዳቸው የተለመ ነው የሚሉም አሉ።
እንዲያውም አብዛኛው ወጣት ከጠቅላይ ሚኒስሯ ጋር የሚያመሳስለኝ ነገር አለ ብሎ እንዲያምን ያደርጋል ሲሉ ይከራከራሉ።
እነዚህ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትሯን ለመደገፍም እየደነሱ ቪድዮ ለጥፈዋል።












