የፊንላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ‘ፓርቲ’ ላይ ሲጨፍሩ መታየታቸው ትችት አስከተለባቸው

የፎቶው ባለመብት, SM
የፊንላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን ሾልኮ በወጣ ቪዲዮ ‘ፓርቲ’ ላይ ሲጨፍሩ መታየታቸው ትችት አስከትሎባቸዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት እየተጋራ ባለው ተንቀሳቃሽ ምስል ጠቅላይ ሚኒስትሯ እና ዝነኛ ፊላንዳውያን ጓደኞቻቸው ሲጨፍሩ እና ሲዘፍኑ ታይተዋል።
ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ከወጣ በኋላ የአገሬው መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከፍተኛ ትችት ተሰንዝሮባቸዋል።
ይባስ ብሎም አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትሯ "የአደንዛዥ እጽ ምረመራ ይደረግላቸው" ሲሉ ጠይቀዋል።
የ36 ዓመቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን አደንዛዥ እጽ አልወሰድኩም ካሉ በኋላ፣ አልኮል መጠጣታቸውን እና በሙሉ ኃይላቸው በፓርቲው ላይ መጨፈራቸውን ግን ተናግረዋል።
የዓለማችን ወጣቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ለጭፈራ ወደ ፓርቲ ቦታ ማቅናትን በምስጢር የሚይዙት ጉዳይ አይደለም። ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሙዚቃ ፌስቲቫሎች ላይ በይፋ ታይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ባለፈው ዓመት እራሳቸውን ለኮቪድ-19 አጋልጠው ወደ ጭፈራ ቤት በመሄዳቸው ይቅርታ ጠይቀው ነበር።
ባለፈው ሳምንት ተዋቂው የጀርመን መጽሔት ቢልድ ሳና ማሪን "የዓለማችን ምርጧ ጠቅላይ ሚኒስትር" ብሏቸው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቪዲዮ እየተቀረጹ መሆኑን እንደሚያውቁ ገልጸው ለሕዝብ ዕይታ መቅረቡ ግን ያበሳጫል ሲሉ ሾልኮ ስለወጣው ተንቀሳቃሽ ምስል አስተያየታቸውን ሲጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ደንሻለሁ፣ ዘፍኛለሁ እንዲሁም ፓርቲ አድርጊያለሁ ሁሉም ሕጋዊ ናቸው። እኔ ወይም በአካባቢዬ አደንዛዥ እጽ በሚወሰድበት ቦታ ሆኜ አላውቅም" ብለዋል የፊንላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ እራሳቸውን ሲከላከሉ፤ "የቤተሰብ ሕይወት አለኝ፣ የሥራ ሕይወት አለኝ፣ እንዲሁም ከጓደኞቼ ጋር የማሳለፈው ነጻ የምሆንበት ጊዜ አለኝ። በእኔ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ከሌሎች ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው" ብለዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ሪካ ፑራ ጠቅላይ ሚኒስትሯ በገዛ ፍቃዳቸው የአደንዛዥ እጽ ምርመራ ያደርጉ ሲሉ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ደግሞ ሌሎች አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች እያሉ ስለ ጭፈራ ማውራቱ ጊዜው አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሯን እና የአገሪቱን መገናኛ ብዙኃን ተችተዋል።
መሪን ከእአአ 2019 መጨረሻ ጀምሮ ፊንላንድን ሲመሩ የቆዩ ሲሆን አሁንም ድረስ ከፓርቲያቸው ጠንካራ ድጋፍ አላቸው።












