የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር አደገኛ ዕፅ አልተጠቀምኩም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከዓለማችን ወጣት የአገር መሪዎች አንዷ የሆኑት የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የአደገኛ ዕፅ ምርመራ ማድረጋቸውን ይፋ አደረጉ።
የ36 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን ምርመራውን እንዲያደርጉ የተገደዱት በዚህ ሳምንት መባቻ በመሸታ ቤት መስመር ባለፈ ሁኔታ ሲጨፍሩ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል መውጣቱን ተከትሎ ነው።
ትናንት ዐርብ አዲስ በወጣ ሌላ ተንቀሳቃሽ ምሥል ደግሞ፣ ሳና ማሪን ከአንድ የፊንላንድ ዕውቅ የሙዚቃ አቀንቃኝ ጋር ተጠጋግተው ሲደንሱ ይታያል።
እነዚህ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ለሕዝብ ከታዩ በኋላ ተቃዋሚዎች ጠቅላይ ሚኒስትሯ የደም ምርመራ እንዲያደርጉ ሲወተውቱ ነበር።
ሳና ማሪን ይህንኑ ጥያቄ በመቀበል የአደገኛ ዕፅ ምርመራ በማድረግ ውጤት እየተጠባበቁ ነው።
የምርመራ ውጤት በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ ይደረጋል።
ወጣቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና በተደጋጋሚ ‘አንዳችም ሕገ ወጥ ተግባር አልፈጸምኩም’ ሲሉ በሔልሲንኪ ለሚገኙ ዘጋቢዎች ተናግረዋል።
‘እንኳንስ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ ይቅርና በአፍላ ዕድሜዬም አደገኛ ዕፅ ያለበት ቦታ ድርሽ ብዬ አላውቅም’ ነው ያሉት፣ ሳና።
ምርመራውን ያደረጉትም በሕዝብ ዘንድ ያለውን ብዥታ ለማጥራት እንደሆነም ተናግረዋል።
በተጨማሪም የምርመራ ውጤቱ ይፋ እስኪደረግ ንጹህ ሆኖ የመገመት መብታቸው እንዲጠበቅም ተማጽነዋል።
አንዳንድ ጋዜጠኞች ለጠቅላይ ሚኒስትሯ በምሽት በሚጨፍሩባቸው ጊዝያት አስቸኳይ የመንግሥት ውሳኔዎች አስፈልገው ቢሆን በስካር መንፈስ ውሳኔ ሰጥተው ያውቁ እንደሆን ጠይቀዋቸው ነበር።
ማሪን ሲመልሱም እንዲህ ዓይነት አስቸኳይ ነገር በሌሊት መጥቶ አያውቅም ብለዋል።
ማሪን በዚህ መሸታ ቤት እየጨፈሩ በነበረበት ወቅት እየተቀረጹ እንደሆነ ያውቁ እንደነበረም ይፋ አድርገዋል።
ነገር ግን ተንቀሳቃሽ ምሥሉ ለሕዝብ ይፋ መደረጉ እንዳላስደሰታቸው አልሸሸጉም።
‘እኔ የመሰለኝ ሰዎች የሥራ ሰዓትንና የመዝናኛ ሰዓትን ለይተው ይመለከታሉ፤ የሰው የግል ድንበር የት ጋ እንደሆነም ይረዳሉ ብዬ አስቤ ነበር’ ብለዋል።
ከዓለም ወጣት መሪዎች አንዷ የሆኑት ማሪን በስፋት የሙዚቃ ፌስቲቫሎች ላይ እየተገኙ ሲጨፍሩ በተደጋጋሚ ታይተው ያውቃሉ።
ባለፈው ሳምንት እንዲያውም ባይልድ የተሰኘ የጀርመን ሚዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሯን ‘የዓለም አራዳዋ መሪ’ በሚል መርጧቸው ነበር።
ባለፈው ሐሙስ ከተለቀቀው ቪዲዮ በኋላ ዐርብ ዕለት ደግሞ ከፊንላንዱ ሞዛቂ ኦላቪ ኡዚቪርታ ጋር ተቀራርበው ሲጨፍሩ የሚያሳይ ሌላ ምሥል ተለቆባቸው ነበር።
አንድ ጋዜጠኛ ጠቅላይ ሚኒስትሯ በዚህ ሞዛቂ እየተሳሙ እንደነበረ ጠይቋቸው ይህንኑ አስተባብለዋል።
‘እየሳመኝ አልነበረም፤ ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ እያወራኝ ነበር፤ ምናልባት ጉንጬን ሳም አድርጎት ሊሆን ይችላል’ ብለዋል።
አክለውም፣ ‘አንድ ወንድ ጉንጬ ላይ ቢስመኝ ጉድ የሚያስብል ነገር አይደለም፤ ለባለቤቴ የምነግረው ትልቅ ጉዳይም ሊሆን አይችልም’ ሲሉ ክስተቱ ይህን ያህል በሚዲያ መራገቡን አጣጥለውታል።
የጠቅላይ ሚኒስትሯ የሰሞኑ ውዝግብ በፊንላድ አዲስ ክርክርን አስነስቷል።
ሚዲያዎች ጉዳዩን ለጥጠውታል ከሚለው ክርክር አንስቶ የአንድ መሪ የግል መብት እስከምን ደረጃ ሊሄድ ይችላል የሚሉት ጉዳዮች በስፋት መነጋገሪያ ሆነዋል።












