ጀርመን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ወታደራዊ አገልግሎት ልትጀምር ነው

ጀርመን ከቀዝቃዛ ዓለም ጦርነት በኋላ የጦር ኃይሏ ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር ቢቀንስም ወታደራዊ አገልግሎትን ግዴታ የሚያደርግ ሕጓን እአአ በ2011 ሰርዛ ነበር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ጀርመን ከቀዝቃዛ ዓለም ጦርነት በኋላ የጦር ኃይሏ ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር ቢቀንስም ወታደራዊ አገልግሎትን ግዴታ የሚያደርግ ሕጓን እአአ በ2011 ሰርዛ ነበር

የጀርመን ፓርላማ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ወታደራዊ አገልግሎትን ለመጀመር የሚያስችል የድጋፍ ድምጽ ሰጠ።

የአገሪቱ ፓርላማ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ሩሲያ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከወረረች በኋላ የአገሪቱን መከላከያ አቅም ለማጠናከር በሚል ነው።

ይህ የአገሪቱ ፓርላማ ውሳኔ ጀርመን ወታደራዊ አቅሟን ለማጠናከር በምትከተለው ፖሊሲ ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው ተብሏል።

ውሳኔው የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ መርዝ የአውሮፓን ጠንካራ መደበኛ ጦር ለመገንባት ሲያደርጉት የነበረውን ግፊት ተከትሎ የመጣ ነው።

ይህንን ለውጥ ተከትሎ 18 ዓመት የሞላቸው ጀርመናውያን በሙሉ ከጥር ወር ጀምሮ የአገሪቱን ጦር ለመቀላቀል ፍላጎቱ እና ፈቃደኝነቱን እንዳላቸው የሚሞሉበት መጠይቅ ይላክላቸዋል።

በመላው ጀርመን 90 በሚደርሱ ከተሞች የሚገኙ ተማሪዎች ግን አርብ ዕለት ውሳኔውን በመቃወም አደባባይ እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በርካታ ጀመርመናውያን አዲሱን ሕግ የሚቃወሙ ወይም በጥርጣሬ የሚመለከቱ ናቸው።

ተቃውሞውን እያደራጁ የሚገኙት ግለሰቦች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፉት ጽሑፍ "የሕይወታችንን ግማሽ ዓመት በጦር ካምፕ ተዘግተን፣ በወታደራዊ ልምምድ እና መግደልን እየተማርን ማሳለፍ አንፈልግም" ብለዋል።

"ጦርነት መጻዒ ዕድል ላይ ምንም ተስፋ አያጭርም እንዲሁም ሕይወታችንን ያወድማል።"

በሐምቡርግ ብቻ 1,500 ሰዎች የተቃውሞ ሠልፉን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን ግን ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት እንዳያስቀሯቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጀርመን ካሏት 323 የሕዝብ እንደራሴዎች መካከል 272ቱ ለውጡን በመደገፍ በአብላጫነት ድምጽ ሰጥተዋል።

ባለፈው ወር ፈረንሳይ ዕድሜያቸው 18 እና 19 ዓመት የሞላቸው ዜጎቿ ለ10 ወር በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ወታደራዊ አገልግሎትን እንዲሰጡ እንደምታደርግ አስታውቃ ነበር።

መንግሥት ወታደራዊ አግልግሎቱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን እና ከሐምሌ 2027 ጀምሮ ግን ሁሉም ዕድሜያቸው 18 ዓመት የሞላ ዜጎች ሊኖር ለሚችል ወታደራዊ አገልግሎት ብቁ መሆናቸውን ለመፈተሽ የጤና ምርመራ እንደሚያደርጉ ተናግሯል።

አጠቃላይ የጤና ምርምራ ማድረግ አስፈላጊ ነበር ያሉት የመከላከያ ሚኒስትሩ ቦሪስ ፒስቶሪየስ፣ ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት ጀርመን "ማን አገሩን ለመከላከል ብቁ ነው? ማን አየደለም" በሚል ጊዜ አታጠፋም ብለዋል።

የጀርመን መከላከያ 182,000 ወታደሮች ያሉት ሲሆን ፒስቶሪየስ ግን ይህንን ቁጥር በሚቀጥለው ዓመት ወደ 20,000 ከፍ ማድረግ ይፈልጋሉ።

የረዥም ጊዜ ዕቅዳቸው ደግሞ በ2030 የአገሪቱን ጦር ቁጥር ወደ 260,000 ከፍ በማድረግ ሲሆን አዲሱን የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ግብ ለመምታት እና የጀርመንን መከላከያ ለማጠናከር 200,000 ተጠባባቂ ኃይል እንዲኖረው ይፈልጋሉ።